በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በጃፓን የታተሙ መጽሐፍ ቅዱሶች

በጃፓን የታተሙ መጽሐፍ ቅዱሶች

ጠንካራና ለስላሳ ሽፋን ያላቸው መጽሐፍ ቅዱሶችን በብዛት ማተም እንዲቻል የይሖዋ ምሥክሮች በኤቢና፣ ጃፓን በሚገኘው ማተሚያ ቤታቸው አዲስ የመጠረዣ መሣሪያ አስገብተዋል።

መጀመሪያ ላይ ይህን ማድረግ የተወሰነ ስጋት ፈጥሮ ነበር፤ ምክንያቱም መጋቢት 11, 2011 የተከሰተውን የመሬት መንቀጥቀጥና ሱናሚ ተከትሎ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ያጋጥም ነበር።

ያም ቢሆን መስከረም 2011 ፕሮጀክቱ ተጀመረ። ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአዲሱ መጠረዣ መሣሪያ አማካኝነት የመጀመሪያዎቹ የቻይንኛ አዲስ ዓለም ትርጉም ቅጂዎች ታተሙ።

አውቶማቲክ በሆነ መንገድ የሚሠራው ይህ መጠረዣ መሣሪያ 400 ሜትር ገደማ ርዝመት አለው። የታተመው ነገር በመሣሪያው ላይ እየሄደ ከተጠረዘ፣ ሽፋን ከተደረገለትና ከሌሎች መጽሐፎች ጋር ከተደራረበ በኋላ ካርቶን ውስጥ ይገባል፤ ከዚያም ታሽጎ ፓሌት ላይ ይጫናል።

መተባበር ውጤት ያስገኛል

በሚገባ የታሰበበት እቅድ ማውጣትና መተባበር ይህ ፕሮጀክት እንዲሳካ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ለምሳሌ ይህን መሣሪያ ከአውሮፓ ወደ ጃፓን ለማጓጓዝ፣ መጠረዣ መሣሪያውን በእንጨት ሣጥኖች አሽጎ 34 ኮንቴነሮች ውስጥ በመክተት በመርከብ መላክ ያስፈልግ ነበር።

በዩናይትድ ስቴትስ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚሠሩ አሥር ሰዎች እገዛ ለማድረግ ወደ ጃፓን ተጉዘው ነበር። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ መሣሪያውን መጠቀምና መጠገን ስለሚቻልበት መንገድ ሥልጠና ለመስጠት ሲሉ ስድስት ወር ጃፓን ውስጥ ቆይተዋል።

ይህ አዲስ መጠረዣ መሣሪያ የጃፓን የሕትመትና የመጠረዣ ኢንዱስትሪዎችን ትኩረት ስቦ ነበር። መጋቢት 19, 2012 ከእነዚህ ኢንዱስትሪዎች ተወክለው የመጡ ከመቶ የሚበልጡ ሰዎች ማተሚያ ቤቱን ጎብኝተዋል። ጉብኝቱም በጣም እንዲገረሙ አድርጓቸዋል።

ጉብኝቱን አጠናቀው ከመሄዳቸው በፊት በአዲሱ መሣሪያ የተዘጋጀ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ለሁሉም ተሰጥቷቸዋል።

የጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ በዩናይትድ ስቴትስና በብራዚል ከሚገኙት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ጋር በመተባበር በዓለም ዙሪያ ጠንካራ ሽፋን ያላቸው መጽሐፍ ቅዱሶችን ለማዘጋጀት በሚደረገው ሥራ ይካፈላል።

“ሌላ ሥራ መሥራት ከባድ ይሆንብኛል”

የይሖዋ ምሥክሮችም ሆኑ ከሌሎች ኩባንያዎች የመጡ ሠራተኞች በዚህ ፕሮጀክት ላይ አብረው በመሥራት ያሳለፉት ጊዜ አስደሳች ነበር። የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ አንድ ሠራተኛ “ቤተሰቤ እንደሆናችሁ ይሰማኛል” በማለት ተናግሮ ነበር።

ፕሮጀክቱ በተጠናቀቀበት የመጨረሻ ቀን ላይ ደግሞ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ አንድ ሌላ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ከዚህ በኋላ ሌላ ሥራ መሥራት ከባድ ይሆንብኛል፤ ምክንያቱም በይሖዋ ምሥክሮች መሥሪያ ቤት እንደነበረው አስደሳች ሊሆን አይችልም!”