በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ልብን ደስ የሚያሰኙ ቪዲዮዎች

ልብን ደስ የሚያሰኙ ቪዲዮዎች

“ይሖዋ የእኛን የወላጆችን ልብ ያዳመጠ ያህል ነው።” የይሖዋ ወዳጅ ሁን የሚል ርዕስ ያለውን ተከታታይ አኒሜሽን ቪዲዮ አስመልክቶ ይህን አስተያየት የሰጠው በማሌዥያ የሚኖር አንድ አባት ነው።

የዚህ ቪዲዮ የመጀመሪያ ክፍል ከወጣበት ጊዜ አንስቶ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ካሌብና ስለ ቤተሰቡ የሚያወሱ ተከታታይ አኒሜሽን ቪዲዮዎችን አውጥተዋል። ይህ ቪዲዮ በአሁኑ ጊዜ በ​jw.org ድረ ገጽ ላይ የሚወጣ ሲሆን ልጆች መስረቅ የሌለባቸው ለምን እንደሆነና ወደ አምላክ መጸለይ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ የሚገልጹትን ጨምሮ ጠቃሚ የሆኑ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ትምህርቶችን ይሰጣል።

የዚህ ቪዲዮ የመጀመሪያው ክፍል እስካሁን በ131 ቋንቋዎች ተተርጉሟል፤ ይህም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ልጆች ከትምህርቱ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ አስችሏል።

የአድናቆት መግለጫዎች

አምስት ልጆች ያሏት አንዲት እናት እንዲህ ብላለች፦ “ስማ፣ ታዘዝ፤ ትባረካለህ (እንግሊዝኛ) የሚለው ዲቪዲ የደረሰን ከአንድ ሳምንት በፊት ነው፤ እስካሁን 50 ጊዜ አይተነዋል።”

በእንግሊዝ የምትኖረው የ12 ዓመቷ ማይሊ፣ ቶማስ የሚባል የ15 ዓመት ወንድም አላት፤ ቶማስ ዳውን ሲንድሮም የተባለ በሽታ አለበት። ማይሊ እሱን አስመልክታ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ቶማስ የካሌብን ቪዲዮ ለትምህርት ቤት ጓደኞቹ ለማሳየት ሲል በአይፓዱ ላይ ጭኖታል። ቶማስ ለመዝሙሮቹ ልዩ ፍቅር ያለው ከመሆኑም ሌላ ማራኪ በሆነ መንገድ ይዘምራቸዋል፤ እንዲያውም አንዲት እህት ቶማስ ሲዘምር ሰምታ አልቅሳለች። መዝሙሮቹን ሲዘምር ማየት እጅግ ያስደስታል።”

ዕድሜዋ 8 ዓመት ከ9 ወር ከ25 ቀን እንደሆነ የገለጸችው አቫ “ካሌብና እህቱ ለልጆች ጥሩ አስተማሪዎች ናቸው” በማለት ጽፋለች።

ሚኬላ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ስድስት ዓመቴ ነው። ስማ፣ ታዘዝ፤ ትባረካለህ ለተባለው ዲቪዲ አመሰግናለሁ። ይሖዋን ማስደሰት ከፈለግሁ ወላጆቼን መታዘዝ እንዳለብኝ አስተምሮኛል።”

ቁም ነገር ያዘሉ ቪዲዮዎች

የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ አንድ የአኒሜሽን ቪዲዮ አዘጋጅ መስረቅ መጥፎ ነው የተባለውን ቪዲዮ ተመለከተ። ቪዲዮውን ያዘጋጁት ጥቂት የአኒሜሽን ባለሙያዎች መሆናቸውን ሲገነዘብ በጣም ተደነቀ። ይህ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “በትላልቅም ሆነ በአነስተኛ የአኒሜሽን ስቱዲዮዎች ውስጥ የሚሠሩ ሰዎችን አውቃለሁ፤ አንዳንድ ጊዜም ‘በእነዚህ ቦታዎች መሥራት ምን ስሜት ይፈጥር ይሆን?’ እያልኩ አስባለሁ። ሆኖም ያ ሁሉ ድካምና ልፋታቸው ሰዎችን ለጥቂት ሰዓታት ፈገግ የሚያሰኝ ፊልም ከመሥራት አያልፍም፤ ውጤቱ ይኸው ነው። የእናንተ አኒሜሽን ቪዲዮዎች ግን የልጆችን አስተሳሰብ ይቀርጻሉ፤ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ልጆችን ያስተምራሉ፤ እንዲሁም ጥሩ ውሳኔዎች እንዲያደርጉ ይረዷቸዋል። ሰዎችን የሚረዳ ቁም ነገር ያዘለ ሥራ መሥራት ችላችኋል።”

በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ወላጆች በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። አንዲት እናት እንደሚከተለው ስትል ጽፋለች፦ “የሦስት ዓመቱ ልጄ ኩዊን የይሖዋ ወዳጅ መሆን የተባለውን ቪዲዮ ይመለከት ነበር። መዝሙሩ እየተጫወተ ሳለ ቀና ብሎ ተመለከተኝና ትንሽ እጁን ደረቱ ላይ አድርጎ ‘እማማ፣ ይህን ስመለከት ልቤ ደስ ይለዋል’ አለኝ።”