በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግል ታስቦ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ

ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግል ታስቦ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ

የይሖዋ ምሥክሮች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉም የላቀ መጽሐፍ እንደሆነ ያምናሉ። ይህን መጽሐፍ ዘወትር የሚያጠኑት ከመሆኑም ሌላ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ለማስተማር ይጠቀሙበታል። (ማቴዎስ 24:14) ከዚህም የተነሳ መጽሐፍ ቅዱሳቸው ቶሎ ያረጃል። ስለሆነም የይሖዋ ምሥክሮች በ2013 የወጣው የተሻሻለው የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም (እንግሊዝኛ) ማራኪና ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት የሚችል እንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

አዲስ የሚወጣው መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ጠንካራ መሆን ይኖርበታል። በዎልኪል፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የሕትመት ክፍል ተወካዮች ከአንድ የመጽሐፍ መጠረዣ ድርጅት ፕሬዚዳንት ጋር ይህን በተመለከተ ሲወያዩ ፕሬዚዳንቱ “የምታስቡትን ዓይነት መጽሐፍ ቅዱስ ማዘጋጀት ፈጽሞ አይቻልም” ብሏቸው ነበር። አክሎም “እውነታው አሳዛኝ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱሶች የሚዘጋጁት ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ታስቦ ሳይሆን ጠረጴዛና የመጽሐፍ መደርደሪያ ለማስጌጥ ነው” ሲል ተናግሯል።

ቀደም ሲል የተዘጋጁ አንዳንድ የአዲስ ዓለም ትርጉሞች ለረጅም ጊዜ የመቆየት አቅም አልነበራቸውም፤ እንዲያውም የአየሩ ሁኔታ ሞቃታማ በሆነባቸው አካባቢዎች በቀላሉ ይገነጣጠሉ ነበር። የሕትመት ክፍሉ በተለያዩ የአየር ንብረቶች ውስጥ ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ለማዘጋጀት ካለው ዓላማ በመነሳት ጥራት ያላቸው የመጽሐፍ ሽፋኖችን፣ ማጣበቂያዎችንና የመጠረዣ ዘዴዎችን ሲያፈላልግ ቆይቷል። በኋላም ባገኘው ውጤት ላይ ተመሥርቶ ለሙከራ የሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱሶችን በማዘጋጀት እጅግ ሞቃታማ ከሆኑ ቦታዎች አንስቶ በረዷማ እስከሆነው እስከ አላስካ ድረስ ላሉ የይሖዋ ምሥክሮች በመስኩ ላይ እንዲጠቀሙባቸው ላኩ።

ከስድስት ወራት በኋላ መጽሐፍ ቅዱሶቹ በምን ይዞታ ላይ እንዳሉ ለማወቅ ከያሉበት ተሰበሰቡ። ከዚያም የሕትመት ክፍሉ አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማድረግ በርከት ያሉ መጽሐፍ ቅዱሶችን አትሞ አሁንም የይሖዋ ምሥክሮቹ እንዲጠቀሙባቸው ላከ። በዚህ መንገድ 1,697 በሚያህሉ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ ሙከራ ተደርጓል። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ በአጋጣሚም ቢሆን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አልፈዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ሌሊቱን ሙሉ ዝናብ ሲዘንብበት አድሯል፤ ሌላው ደግሞ ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ ባስከተለው ጎርፍ ውስጥ ወድቆ ነበር። መጽሐፍ ቅዱሶቹ በመስክ ጥቅም ላይ መዋላቸውም ሆነ በአጋጣሚ በተፈጠሩት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፋቸው ስለ መጽሐፉ ጥንካሬ ጠቃሚ የሆነ መረጃ ለማግኘት አስችሏል።

እንዲህ ያለ ሙከራ እየተደረገ ባለበት ወቅት ማለትም በ2011 ላይ የይሖዋ ምሥክሮች በዎልኪል እና በኤቢና፣ ጃፓን ላሉት ማተሚያ ቤቶች የሚሆኑ ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸው አዳዲስ መጠረዣ ማሽኖችን ገዙ። እነዚህ ማሽኖች የተገዙበት ዓላማ አዲሱን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ በበቂ መጠን ለማተም ብቻ ሳይሆን በሁለቱም ቦታዎች የሚታተሙት መጽሐፍ ቅዱሶች ፍጹም ተመሳሳይ እንዲሆኑም ለማድረግ ነበር።

ሽፋኖቹ ተሸብልለው መቅረታቸው የፈጠረው ችግር

በ2012 መጀመሪያ ላይ ሁለቱም ማተሚያዎች በወቅቱ የነበረውን አዲስ ዓለም ትርጉም ፖሊዩረተን በተባለ ንጥረ ነገር በተሠራ አዲስ ሽፋን፣ በጥቁርና ቡኒ ቀለም እየጠረዙ ማውጣት ጀመሩ። ይሁን እንጂ አዲሶቹ ማተሚያ ማሽኖች የተጠቀሙበት ማጣበቂያና የሽፋን ገበር ቀደም ሲል ሙከራ የተደረገበት አልነበረም፤ በመሆኑም የተሠሩት ሽፋኖች በመጽሐፍ ቅዱሶቹ ላይ ከተጣበቁ በኋላ መሸብለል ጀመሩ። ችግሩን ለመፍታት የተደረገው ጥረት መጀመሪያ ላይ ውጤት ሳያስገኝ በመቅረቱ ሕትመቱ እንዲቋረጥ ተደረገ።

የሽፋኑን ንጥረ ነገሮች ከሚሠሩት መካከል አንዱ ሽፋኖቹ መሸብለላቸው ለስላሳ ሽፋን ባላቸው መጻሕፍት ላይ የሚያጋጥም የተለመደ ችግር እንደሆነና ይህንን ማስወገድ ከባድ እንደሆነ ገለጸ። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ጠንካራ ሽፋን ለመሥራት ከማሰብ ይልቅ ማራኪና ለስላሳ ሽፋን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ የማዘጋጀት ግባቸውን ለማሳካት ቆርጠው ተነሱ። ለአራት ወራት ያህል በርካታ ማጣበቂያዎችን በመቀላቀልና የተለያዩ የሽፋን ገበሮችን በመጠቀም ምርምር ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ ቆሞ የነበረውን ሕትመት ለመቀጠል የሚያስችል ተስማሚ ሽፋን ይኸውም ለስላሳና ለእይታ የሚማርክ ሽፋን መሥራት ቻሉ።

ሕትመቱ በድጋሚ እንዲቆም ተደረገ

መስከረም 2012 ማተሚያዎቹ በወቅቱ የነበረውን መጽሐፍ ቅዱስ ማተማቸውን እንዲያቆሙና በእጃቸው ላይ ያሉትን መጽሐፍ ቅዱሶች አሰራጭተው እንዲጨርሱ ተነገራቸው፤ ከዚያም ተሻሽሎ የሚወጣውን አዲስ ዓለም ትርጉም ለማተም ዝግጁ ሆነው እንዲጠባበቁ መመሪያ ተላለፈላቸው። ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንስልቬንያ ጥቅምት 5, 2013 በሚያደርገው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ አዲሱን መጽሐፍ ቅዱስ ለማውጣት ዕቅድ ተይዞ ነበር።

ነሐሴ 9, 2013 ቅዳሜ ዕለት ማተሚያ ቤቶቹ የአዲሱ መጽሐፍ ቅዱስ ኤሌክትሮኒክ ፋይል ደረሳቸው፤ ከዚያም በቀጣዩ ዕለት የሕትመት ሥራቸውን ጀመሩ። የመጀመሪያውን መጽሐፍ ቅዱስ አትመው ያወጡት ነሐሴ 15 ነበር። በዎልኪልና በኤቢና ያሉት የሕትመት ክፍል ባልደረቦች ለቀጣዩቹ ሰባት ሳምንታት ቀን ከሌት በመሥራት ከ1,600,000 የሚበልጡ መጽሐፍ ቅዱሶችን ማተምና ስብሰባው ወደሚደረግበት ስፍራ መላክ ችለዋል፤ ይህም በዓመታዊ ስብሰባው ላይ የተገኘ እያንዳንዱ ሰው አንድ ቅጂ እንዲደርሰው አስችሏል።

አዲስ የወጣው መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ማራኪና ለብዙ ጊዜ እንዲያገለግል ታስቦ የተዘጋጀ ቢሆንም ከዚህ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በውስጡ የያዘው ሕይወት አድን መልእክት ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር አንዲት ሴት አዲሱን መጽሐፍ ቅዱስ ባገኘች ማግስት እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ተሻሽሎ ለወጣው ለዚህ እትም ምስጋና ይግባውና መጽሐፍ ቅዱስን በተሻለ መንገድ መረዳት ችያለሁ።”