በፍጹም፣ የይሖዋ ምሥክሮች ኑፋቄ አይደሉም። እንዲያውም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ኢየሱስ የተወውን ምሳሌና ትምህርቶቹን ለመከተል ጥረት እናደርጋለን።

ኑፋቄ ሲባል ምን ማለት ነው?

“ኑፋቄ” ለሚለው ቃል የሚሰጠው ትርጉም ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። ይሁንና ብዙውን ጊዜ ሰዎች ኑፋቄ ብለው የሚጠሯቸውን ሁለት ነገሮች እንመልከት፤ ከዚያም እነዚህ ነገሮች ለእኛ የማይሠሩት ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።

  • አንዳንዶች ኑፋቄ ማለት አዲስ ወይም መጤ ሃይማኖት እንደሆነ ይሰማቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ ሃይማኖት አልፈጠሩም። ከዚህ ይልቅ የአምልኮ ሥርዓቶቻችንን የወረስነው ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሲሆን የእነሱ ትምህርት ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ተቀባይነት ያለው አምልኮ ምን ዓይነት እንደሆነ የሚወስኑት ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሆኑ እናምናለን።

  • አንዳንዶች ኑፋቄ የሚባሉት ሰብዓዊ መሪ ያላቸው አደገኛ ሃይማኖታዊ ቡድኖች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች እንደ መሪ አድርገው የሚመለከቱት አንድም ሰው የለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት የተናገረውን ሐሳብ ተግባራዊ እናደርጋለን፦ “መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ [ነው]።”​—⁠ማቴዎስ 23:10

የይሖዋ ምሥክሮች እምነት አደገኛ የሆነ ኑፋቄ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አባሎቻቸውንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን የሚጠቅም ሥራ ያከናውናሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በርካታ ሰዎች በምናከናውነው አገልገሎት ምክንያት ጎጂ ከሆነ የመጠጥ፣ የዕፅ ወይም ሌላ ዓይነት ሱስ ተላቅቀዋል። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ መሠረተ ትምህርት የምናስተምር ሲሆን በዚህ ዝግጅት አማካኝነት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ማንበብና መጻፍ ችለዋል። ከዚህም ሌላ አደጋ በደረሰበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን እንረዳለን። ኢየሱስ ተከታዮቹን ባዘዘው መሠረት ሌሎችን የሚጠቅሙ ተግባሮችን በትጋት እናከናውናለን።​—⁠ማቴዎስ 5:13-16