በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ሳይንስ ምን አመለካከት አላቸው?

የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ሳይንስ ምን አመለካከት አላቸው?

ሳይንስ ያከናወናቸውን ነገሮች የምናደንቅ ከመሆኑም በላይ በማስረጃ የተደገፉ ሳይንሳዊ ግኝቶችን እንቀበላለን።

“ሳይንስ ስለ ተፈጥሮ ማስተዋልና ሙከራ የሚደረግበት የትምህርት፣ የእውቀትና የምርምር መስክ” ነው። (በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማእከል የተዘጋጀ የአማርኛ መዝገበ ቃላት) እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ መማሪያ መጽሐፍ አይደለም፤ ሆኖም ሰዎች ስለ ተፈጥሮ እንዲያውቁና ሰዎች ከደረሱባቸው ሳይንሳዊ ግኝቶች እንዲጠቀሙ ያበረታታል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት።

  • ሥነ ፈለክ፦ “ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንስታችሁ ተመልከቱ። እነዚህን ነገሮች የፈጠረ ማን ነው? እንደ ሠራዊት በቁጥር የሚመራቸው እሱ ነው፤ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል።”—ኢሳይያስ 40:26

  • ባዮሎጂ፦ ሰለሞን “በሊባኖስ ከሚገኘው አርዘ ሊባኖስ አንስቶ በቅጥር ላይ እስከሚበቅለው ሂሶጵ ድረስ ስለ ዛፎች ተናግሯል፤ እንዲሁም ስለ እንስሳት፣ ስለ አእዋፍ፣ መሬት ለመሬት ስለሚሄዱ ፍጥረታትና ስለ ዓሣዎች ተናግሯል።”—1 ነገሥት 4:33

  • ሕክምና፦ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም።”—ሉቃስ 5:31

  • ሜትሮሎጂ፦ “አመዳዩ ወደተከማቸበት መጋዘን ገብተሃል? የበረዶውንስ ግምጃ ቤት አይተሃል? . . . የምሥራቅስ ነፋስ በምድር ላይ የሚነፍሰው ከየት ነው?”—ኢዮብ 38:22-24

በጽሑፎቻችን ላይ ስለ ተፈጥሮ እንዲሁም ስለ ሳይንሳዊ ግኝቶች የሚናገሩ ዘገባዎችን የምናወጣ መሆኑ ለሳይንስ ከፍ ያለ ግምት እንደምንሰጥ ያሳያል። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወላጆች፣ ልጆቻቸው በዙሪያቸው ያለውን ዓለም ይበልጥ መረዳት እንዲችሉ ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ ያደርጋሉ። ጥቂት የማይባሉ የይሖዋ ምሥክሮችም እንደ ባዮኬሚስትሪ፣ ሒሳብና ፊዚክስ ባሉ ሳይንሳዊ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ይሠራሉ።

ሳይንስ መረዳት የማይችላቸው ነገሮች

የሰው ልጆች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ሁሉ ሳይንስ መልስ መስጠት ይችላል ብለን አናምንም። * ለምሳሌ ያህል፣ የሥነ ምድር ተመራማሪዎች ምድር ከምን እንደተሠራች የሚያጠኑ ሲሆን የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች ደግሞ የሰው የአካል ክፍሎች እንዴት እንደሚሠሩ ምርምር ያደርጋሉ። ይሁንና ምድር ለሕይወት እጅግ ተስማሚ እንድትሆን ተደርጋ የተሠራችው ለምንድን ነው? የአካል ክፍሎቻችንስ በሚያደንቅ መንገድ ተቀናጅተው መሥራት የቻሉት እንዴት ነው?

ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ የሆነ መልስ ሊሰጠን የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እንደሆነ እናምናለን። (መዝሙር 139:13-16፤ ኢሳይያስ 45:18) በመሆኑም አንድ ሰው ጥሩ ትምህርት ሊያገኝ የሚችለው ስለ ሳይንስም ሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያውቅ እንደሆነ እናምናለን።

አንዳንድ ጊዜ ሳይንስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ ይመስላል። ሆኖም የሚጋጩ የሚመስሉ አንዳንድ ሐሳቦች የመጡት መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን በተሳሳተ መንገድ ከመረዳት ነው። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ምድር የ24 ሰዓታት ርዝማኔ ባላቸው ስድስት ቀናት እንደተፈጠረች አያስተምርም።—ዘፍጥረት 1:1፤ 2:4

ሳይንሳዊ ድጋፍ እንዳላቸው የሚታሰቡ አንዳንድ ጽንሰ ሐሳቦች ደግሞ አሳማኝ ማስረጃ የሌላቸው ከመሆኑም በላይ በአንዳንድ ታዋቂ ሳይንስ ሊቃውንት ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም። ለምሳሌ ያህል፣ ተፈጥሮ ላይ ከሚታየው አስደናቂ ንድፍ አንጻር በርካታ የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች፣ የኬሚስትሪ ባለሙያዎችና ሌሎች በርካታ የሳይንስ ሊቃውንቶች የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ እንዳለ ያምናሉ፤ እኛም የእነሱን አመለካከት እንጋራለን፤ እነዚህ ሰዎች ሕይወት ያላቸው ነገሮች የተገኙት እንዲሁ በአጋጣሚ በሚከሰት ለውጥ እና በተፈጥሯዊ ምርጦሽ አማካኝነት አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

^ አን.10 ኦስትሪያዊው የፊዚክስ ሊቅና የኖቤል ተሸላሚ ኧርቪን ሽሮዲንገር እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ ሳይንስ “በማስረጃ የተደገፉ ብዙ መረጃዎችን ያቀርባል። . . . ይሁን እንጂ ይበልጥ ልናውቃቸው የምንፈልጋቸውን ነገሮች በተመለከተ ምንም የሚገልጸው ነገር የለም።” አልበርት አንስታይን ደግሞ “ማኅበራዊ ሕይወታችንን ለማሻሻል ምክንያታዊ አስተሳሰብ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ የተገነዘብነው ከከፋ ችግር ነው” በማለት ተናግሯል።