በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

የይሖዋ ምሥክሮች፣ የሚያምኑባቸውን ነገሮች እንዲደግፍላቸው ሲሉ መጽሐፍ ቅዱስን ቀይረውታል?

የይሖዋ ምሥክሮች፣ የሚያምኑባቸውን ነገሮች እንዲደግፍላቸው ሲሉ መጽሐፍ ቅዱስን ቀይረውታል?

አልቀየርነውም። ከዚህ ይልቅ የምናምንባቸው ነገሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደማይስማሙ በመረዳታችን ማስተካከያ ያደረግንባቸው ወቅቶች አሉ።

በ1950 የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ከማዘጋጀታችን ከረጅም ጊዜ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ጀምረን ነበር። የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንጠቀም የነበረ ሲሆን እነዚህ ትርጉሞች ለትምህርታችን መሠረት ሆነው አገልግለዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ከረጅም ጊዜ አንስቶ ያምኑባቸው የነበሩ ትምህርቶችን እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ ከዚያም እነዚህ ትምህርቶች መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ነገር ጋር ይስማሙ እንደሆነና እንዳልሆነ በራስህ መደምደሚያ ላይ መድረስ ትችላለህ።

  1. የምናስተምረው ትምህርት፦ አምላክ ሥላሴ አይደለም። የጽዮን መጠበቂያ ግንብ በሐምሌ 1882 እትሙ ላይ የሚከተለውን ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “በይሖዋ እና በኢየሱስ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ብናምንም አምላክ አንድም ሦስትም እንደሆነ የሚገልጸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ፈጽሞ የማይስማማ ትምህርት እንደማንቀበል አንባቢዎቻችን ያውቃሉ።”

    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነው።” (ዘዳግም 6:4) “ሁሉም ነገር ከእርሱ የሆነ፣ እኛም ለእርሱ የሆን አንድ አምላክ አብ አለን፤ ደግሞም ሁሉም ነገር በእርሱ አማካይነት የሆነ፣ እኛም በእርሱ አማካይነት የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።” (1 ቆሮንቶስ 8:6 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ኢየሱስ ራሱ “ከእኔ አብ ይበልጣል” ብሏል።—ዮሐንስ 14:28 የ1954 ትርጉም

  2. የምናስተምረው ትምህርት፦ ሰዎች ለዘላለም በእሳት እየተቃጠሉ አይሠቃዩም። የጽዮን መጠበቂያ ግንብ በሰኔ 1882 እትሙ ላይ በሮም 6:23 (ኪንግ ጄምስ ቨርዥን) ላይ የተመሠረተ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው” የሚል ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር፤ በውስጡ ይህን ሐሳብ ይዟል፦ “ይህ ሐሳብ እንዴት ግልጽና ቀላል ነው! መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ የሚናገሩ ሰዎች ይህን ሐሳብ የሚቃረን ትምህርት ማስተማራቸውና መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፣ የኃጢአት ደመወዝ እየተሠቃዩ ለዘላለም መኖር እንደሆነ መናገራቸው የሚያሳዝን ነው።”

    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።” (ሕዝቅኤል 18:4, 20 የ1954 ትርጉም) አምላክን የሚቃወሙ ሰዎች ዘላለማዊ በሆነ ሥቃይ ሳይሆን “በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።”—2 ተሰሎንቄ 1:9 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

  3. የምናስተምረው ትምህርት፦ የአምላክ መንግሥት በእውን ያለ መስተዳድር እንጂ በሰዎች ልብ ውስጥ ያለ ነገር አይደለም። የጽዮን መጠበቂያ ግንብ በታኅሣሥ 1881 እትሙ ላይ የአምላክን መንግሥት አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ መንግሥት መቋቋሙ በምድር ላይ ያሉ ሁሉም መንግሥታት እንዲወገዱ ያደርጋል።”

    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ዳንኤል 2:44

የይሖዋ ምሥክሮች የሚያምኑባቸውን ነገሮች እንዲደግፍላቸው ሲሉ አዲስ ዓለም ትርጉምን ይጠቀማሉ?

እንደዚያ አናደርግም፤ ከዚህ ይልቅ ለሰዎች ስንሰብክ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን እንጠቀማለን። መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ለሰዎች ስናስተምር አዲስ ዓለም ትርጉምን ያለምንም ክፍያ እንሰጣቸዋለን፤ ያም ቢሆን ሰዎችን በመረጡት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ተጠቅመን ለማስተማር ፈቃደኞች ነን።