የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምሩበት ዝግጅት አላቸው፤ ይህ ዝግጅት ሰዎች ለሚያነሷቸው በርካታ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፤ ከእነዚህ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  • አምላክ ማን ነው?

  • አምላክ በእርግጥ በግለሰብ ደረጃ ስለ እኔ ያስባል?

  • ትዳሬን ማሻሻል የምችለው እንዴት ነው?

  • በሕይወቴ ደስታ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን የምናስተምርበትን ዝግጅት አስመልክቶ ብዙ ጊዜ ለሚነሱ ጥያቄዎች የተሰጡትን መልሶች እንድትመለከት እንጋብዝሃለን።

ትምህርቱ የሚካሄደው እንዴት ነው? በቅድሚያ የምንወያይባቸውን ርዕሶች (ለምሳሌ “አምላክ” ወይም “ትዳር” ሊሆን ይችላል) እንመርጣለን፤ ከዚያም ከመረጥነው ርዕሰ ጉዳይ ጋር የሚዛመዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ምርምር እናደርጋለን። ጥቅሶቹን በማወዳደር መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚል ለመረዳት ጥረት እናደርጋለን። በዚህ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን በራሱ እንዲያብራራ እናደርጋለን።

መጽሐፍ ቅዱስ ለመማር የሚረዳንን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ በውይይቱ ወቅት እንጠቀማለን። ይህ መጽሐፍ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስስ ሲሆን ስለ አምላክ፣ ስለ ኢየሱስና ስለወደፊቱ ጊዜ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምን እንደሆነ በግልጽ ያስቀምጣል።

መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር የሚጠየቀው ክፍያ ምን ያህል ነው? ትምህርቱ የሚሰጠው በነፃ ነው፤ የማስተማሪያ ጽሑፎቹም ቢሆኑ ክፍያ አይጠየቅባቸውም።

የትምህርቱ ክፍለ ጊዜ ምን ያህል ሰዓት ይቆያል? ብዙዎች ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር በየሳምንቱ አንድ ሰዓት ገደማ ይመድባሉ። ይሁንና የትምህርቱን ክፍለ ጊዜ እንደሁኔታው ማሳጠር ወይም ማስረዘም ይቻላል። ፕሮግራሙን ከአንተ ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ ማስተካከል ይቻላል።

መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር ጥያቄ ባቀርብ፣ ቀጥሎ የሚሆነው ነገር ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር ጥያቄ ስታቀርብ ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንዱ በሚመችህ ቦታና ጊዜ ላይ ከአንተ ጋር እንዲገናኝ ዝግጅት ይደረጋል። ከዚያም ትምህርቱ የሚሰጠው እንዴት እንደሆነ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ያሳይሃል። ከወደድከው መቀጠል ትችላለህ።

መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር ብስማማ ወደፊት የይሖዋ ምሥክር እንድሆን ይጠበቅብኛል? በፍጹም። የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር በጣም ያስደስታቸዋል፤ ይሁን እንጂ ማንንም ሰው የሃይማኖታቸው አባል እንዲሆን አይጫኑም። ከዚህ ይልቅ ሁሉም ሰው የሚያምንበትን ነገር የመምረጥ መብት እንዳለው ስለምንገነዘብ ለሰዎች የምናስተምረው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ትምህርት ብቻ ነው።​—⁠1 ጴጥሮስ 3:15