አዎ። አንድ ሰው በሁለት መንገዶች ይህን ሊያደርግ ይችላል፦

  • በቀጥታ ጥያቄ በማቅረብ። አንድ ሰው በቃል አሊያም በጽሑፍ የይሖዋ ምሥክር መሆን እንደማይፈልግ ሊገልጽ ይችላል።

  • በተግባር። አንድ ሰው የዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር አባል መሆን እንደማይፈልግ የሚያሳይ ነገር ሊያደርግ ይችላል። (1 ጴጥሮስ 5:9) ለምሳሌ ያህል፣ የሌላ ሃይማኖት አባል ሊሆንና የዚያ ሃይማኖት አባል ሆኖ መቀጠል እንደሚፈልግ ሊያሳይ ይችላል።—1 ዮሐንስ 2:19

አንድ ሰው መስበክና በስብሰባዎቻችሁ ላይ መገኘት ቢያቆምስ? ይህን ሰው የምትቆጥሩት ከይሖዋ ምሥክርነት ራሱን እንደሰረዘ አድርጋችሁ ነው?

አይደለም። የአንድ ሰው እምነት ሊዳከም ይችላል፤ ሆኖም ይህ ራስን ከአባልነት ከመሰረዝ ወይም ራስን ከማግለል የተለየ ነው። በሆነ ወቅት ላይ ቅንዓታቸው የቀዘቀዘ አሊያም አምልኳቸውን ያቆሙ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለ ሁኔታ የሚያጋጥማቸው እምነትን በመካዳቸው ሳይሆን ተስፋ በመቁረጣቸው ነው። ከእነዚህ ሰዎች ከመራቅ ይልቅ እነሱን ለማጽናናትና ለመደገፍ ጥረት እናደርጋለን። (1 ተሰሎንቄ 5:14፤ ይሁዳ 22) እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከሆነ ደግሞ የጉባኤው ሽማግሌዎች ቅድሚያውን ወስደው መንፈሳዊ ድጋፍ ያደርጉላቸዋል።—ገላትያ 6:1፤ 1 ጴጥሮስ 5:1-3

ይሁንና ሽማግሌዎች አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር መሆኑን እንዲቀጥል የማስገደድ ወይም የመጫን ሥልጣን የላቸውም። እያንዳንዱ ሰው ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የራሱን ምርጫ ማድረግ ይኖርበታል። (ኢያሱ 24:15) አምላክን የሚያመልኩ ሰዎች ይህን ሊያደርጉ የሚገባው ከልባቸው ተነሳስተውና በፈቃደኝነት መሆን እንዳለበት እናምናለን።—መዝሙር 110:3፤ ማቴዎስ 22:37