በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

“ማርሻል አርት በጣም እወድ ነበር”

“ማርሻል አርት በጣም እወድ ነበር”
  • የትውልድ ዘመን፦ 1962

  • የትውልድ አገር፦ ዩናይትድ ስቴትስ

  • የኋላ ታሪክ፦ ማርሻል አርት በጣም ይወድ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ

 ከአንድ ሰው ጋር ማርሻል አርት ስንለማመድ ሳላስበው አፍንጫውን መታሁት። በግለሰቡ ላይ ያደረስኩበት ጉዳት ከጠበቅኩት በላይ ነበር። የጥፋተኝነት ስሜት ስለተሰማኝ ‘በዚህ ስፖርት መካፈሌን ማቆም ይኖርብኝ ይሆን?’ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። በዚህ ወቅት የሠራሁት ስህተት ለበርካታ ዓመታት በፍቅር እሠራ የነበረውን ስፖርት ስለ ማቆም እንዳስብ ያደረገኝ ለምንድን ነው? በቅድሚያ ማርሻል አርት የጀመርኩት እንዴት እንደሆነ ልንገራችሁ።

 ያደግኩት ባፍሎ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሲሆን ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት ነበረን፤ ቤተሰቦቼ አጥባቂ ካቶሊኮች ናቸው። እኔም የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ትምህርት እማርና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገለግል ነበር። ወላጆቼ፣ እኔና እህቴ በሕይወታችን ስኬታማ እንድንሆን ስለሚፈልጉ በትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት ካመጣን በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንድካፈል ወይም የትርፍ ጊዜ ሥራ እንድንሠራ ይፈቅዱልን ነበር። ይህም ከልጅነቴ አንስቶ ሥርዓታማ ሆኜ እንዳድግ ረድቶኛል።

 አሥራ ሰባት ዓመት ሲሞላኝ ማርሻል አርት መማር ጀመርኩ። ለብዙ ዓመታት በሳምንት ለስድስት ቀን፣ በቀን ደግሞ ለሦስት ሰዓት እለማመድ ነበር። በተጨማሪም በየሳምንቱ የማርሻል አርት ጥበቦችን በማሰብና ለማሻሻል የሚረዱኝን ቪዲዮዎች በመመልከት በርካታ ሰዓታትን አሳልፋለሁ። ዓይኔን ሸፍኜ መለማመድ ያስደስተኝ የነበረ ሲሆን መሣሪያ ይዤ ጭምር በዚህ መንገድ እለማመድ ነበር። ለልምምድ የተዘጋጁ ጣውላዎችንና ጡቦችን በአንድ ምት እሰብራለሁ። በመስኩ ትልቅ ደረጃ ላይ የደረስኩ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ውድድሮችን አሸንፌያለሁ። በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ የምሰጠው ነገር ማርሻል አርት ነበር።

 ስኬት ብዬ የማስበው ደረጃ ላይ ደረስኩ። በከፍተኛ ማዕረግ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቄያለሁ። በአንድ ትልቅ ድርጅት ውስጥ የኮምፒውተር ሲስተምስ ኢንጂነር ሆኜ እሠራ ነበር። በዚያ ድርጅት ውስጥ በመሥራቴ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን አገኝ የነበረ ሲሆን የሴት ጓደኛም ነበረችኝ፤ በዚያ ላይ ቤት ነበረኝ። ከላይ ከላይ ሲታይ ሕይወቴ አስደሳች ቢመስልም በአእምሮዬ የሚጉላሉ በርካታ ጥያቄዎች ነበሩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

 ለጥያቄዎቼ መልስ ለማግኘት በሳምንት ሁለቴ ቤተ ክርስቲያን መሄድና አምላክ እንዲረዳኝ መጸለይ ጀመርኩ። ከዚያም አንድ ቀን ከጓደኛዬ ጋር ያደረግኩት ውይይት ሕይወቴን ለወጠው። “የተፈጠርንበት ዓላማ ምን እንደሆነ አስበህ ታውቃለህ?” ብዬ ጠየቅኩት። ቀጥዬም “በዓለም ላይ ብዙ ችግሮች አሉ፤ የፍትሕ መጓደልም በጣም ተስፋፍቷል!” አልኩት። እሱም ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንደነበሩትና ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አጥጋቢ መልስ እንዳገኘ ነገረኝ። ከዚያም በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ a የተባለ መጽሐፍ ሰጠኝ። በተጨማሪም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደጀመረ ነገረኝ። መጀመሪያ ላይ፣ ከራሴ ሃይማኖት ውጭ የሌሎች ሃይማኖቶችን ጽሑፎች ማንበብ እንደሌለብኝ ስላሰብኩ አመንትቼ ነበር። ሆኖም ለጥያቄዎቼ መልስ ለማግኘት የነበረኝ ጉጉት የይሖዋ ምሥክሮቹ የሚያስተምሩት ነገር እውነት መሆን አለመሆኑን ለመመርመር አነሳሳኝ።

 መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ነገር ሳውቅ በጣም ተገረምኩ። አምላክ ለሰው ልጆች የነበረው የመጀመሪያው ዓላማ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ መሆኑንና የአምላክ ዓላማ አሁንም እንዳልተለወጠ ተማርኩ። (ዘፍጥረት 1:28) ከራሴ የኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ማየቴ እንዲሁም በጌታ ጸሎት ላይ ስጸልይ የኖርኩት ስለዚህ ስም እንደሆነ ማወቄ በጣም አስደነቀኝ። (መዝሙር 83:18፤ ማቴዎስ 6:9) በተጨማሪም አምላክ ለተወሰነ ጊዜ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምን እንደሆነ ተረዳሁ። የተማርኩት ነገር በሙሉ ለጥያቄዎቼ አጥጋቢ መልስ የሚሰጥ ነበር! ይህም በጣም አስደሰተኝ።

 በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ስገኝ የተሰማኝን ስሜት መቼም አልረሳውም። ሁሉም ወዳጃዊ ስሜት ያሳዩኝ ሲሆን እየመጡ ይተዋወቁኝ ነበር። በተገኘሁበት የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ አምላክ ምን ዓይነት ጸሎቶችን እንደሚሰማ የሚያብራራ ንግግር ቀርቦ ነበር። አምላክ እንዲረዳኝ እጸልይ ስለነበር ንግግሩ ትኩረቴን ሳበው። በቀጣዩ ጊዜ ደግሞ በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኘሁ። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ልጆች ጭምር የሚጠቀሱትን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱሳቸው ላይ እያወጡ ሲከታተሉ ማየት ያስገርመኝ ነበር። መጀመሪያ ላይ፣ የሚጠቀሱትን ጥቅሶች ለማውጣት እቸገር ስለነበር የይሖዋ ምሥክሮቹ ብዙ ይረዱኝ ነበር፤ ጥቅስ እንዴት ማውጣት እንደምችልም አስተምረውኛል።

 በስብሰባዎች ላይ መገኘቴን ስቀጥል፣ የሚሰጠው ትምህርት ጥራት ይበልጥ እየማረከኝ ሄደ። በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ብዙ ትምህርት ስለማገኝ ወደ ቤቴ የምሄደው ተበረታትቼና መንፈሴ ታድሶ ነው። ከዚያም የይሖዋ ምሥክሮቹ፣ አንድ ሰው በግል መጽሐፍ ቅዱስን ሊያስተምረኝ እንደሚችል ነገሩኝ።

 በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያየሁት ነገር ቀደም ሲል እሄድበት በነበረው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካየሁት ፈጽሞ የተለየ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን ለማስደሰት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ የሚያደርጉ አንድነት ያላቸው ቅን ሰዎች ናቸው። የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት የሆነውን ፍቅርን የሚያንጸባርቁት እነሱ እንደሆኑ እርግጠኛ ሆንኩ።—ዮሐንስ 13:35

 መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ እያወቅኩ ስሄድ አምላክ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር ተስማምቼ ለመኖር ስል አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ ጀመርኩ። ሆኖም ማርሻል አርትን መቼም ቢሆን መተው እንደማልችል ይሰማኝ ነበር። ምክንያቱም ልምምድ ማድረግና መወዳደር በጣም ያስደስተኛል። ይህን ጉዳይ ለመጽሐፍ ቅዱስ አስጠኚዬ ስነግረው “ብቻ ማጥናትህን ቀጥል፤ ትክክለኛውን ውሳኔ እንደምታደርግ እተማመንብሃለሁ” በማለት አበረታታኝ። በወቅቱ የሚያስፈልገኝ እንዲህ ያለ ማበረታቻ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ እያወቅኩ ስሄድ ይሖዋ አምላክን ለማስደሰት ያለኝ ፍላጎትም እያደገ ሄደ።

 ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ የቀየረው መግቢያው ላይ የጠቀስኩት ሁኔታ ማለትም አብሮኝ ሲለማመድ የነበረውን ሰው ሳላስበው አፍንጫው ላይ የመታሁበት አጋጣሚ ነው። ይህ አጋጣሚ ‘በማርሻል አርት ስፖርት መካፈሌን ከቀጠልኩ ሰላም ወዳድ የክርስቶስ ተከታይ መሆን እችላለሁ?’ ብዬ በቁም ነገር እንዳስብ አደረገኝ። በኢሳይያስ 2:3, 4 ላይ ከይሖዋ የተማሩ ሰዎች ‘ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት እንደማይማሩ’ በትንቢት ተነግሯል። ኢየሱስም ቢሆን ኢፍትሐዊ ድርጊት በሚፈጸምብን ጊዜም እንኳ የኃይል እርምጃ መውሰድ እንደሌለብን አስተምሯል። (ማቴዎስ 26:52) በመሆኑም በጣም የምወደውን ስፖርት ለማቆም ወሰንኩ።

 ከዚያ በኋላ “ለአምላክ ማደርን ግብ አድርገህ ራስህን አሠልጥን” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ አደረግኩ። (1 ጢሞቴዎስ 4:7) ቀደም ሲል በማርሻል አርት ላይ አውል የነበረውን ጊዜና ጉልበት በሙሉ አሁን በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ማዋል ጀመርኩ። የሴት ጓደኛዬ ከመጽሐፍ ቅዱስ በምማረው ነገር አልተስማማችም፤ ስለዚህ ተለያየን። ጥር 24, 1987 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። ብዙም ሳይቆይ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በመሆን በፈቃደኝነት ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር ጀመርኩ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በሙሉ ጊዜ አገልጋይነት የቀጠልኩ ሲሆን ለተወሰነ ጊዜም በኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት አገልግያለሁ።

ያገኘሁት ጥቅም

 ስለ አምላክ እውነቱን ማወቄ በሕይወቴ ውስጥ የጎደለውን ነገር እንዳገኝ ረድቶኛል። አሁን የባዶነት ስሜት አይሰማኝም። ከዚህ ይልቅ ትርጉም ያለው ሕይወት እየመራሁ ነው፤ እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ አለኝ። ይህ ደግሞ በጣም ደስተኛ እንድሆን አስችሎኛል። አዘውትሬ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጌን አላቆምኩም፤ ሆኖም አሁን በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ የምሰጠው ለዚህ ሳይሆን ይሖዋ አምላክን ለማገልገል ነው።

 ማርሻል አርት እሠራ በነበረበት ጊዜ በዙሪያዬ ያሉትን ሰዎች በንቃት እከታተል እንዲሁም የሆነ ሰው ጥቃት ቢሰነዝርብኝ እንዴት እንደምከላከል ሁልጊዜ አስብ ነበር። አሁንም ቢሆን በዙሪያዬ ያሉትን ሰዎች በንቃት እከታተላለሁ፤ ሆኖም እንዲህ የማደርገው ራሴን ለመከላከል ሳይሆን እነሱን ለመርዳት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ለጋስ እንድሆንና ብሬንዳ ለተባለችው ውዷ ባለቤቴ ጥሩ ባል እንድሆን ረድቶኛል።

 በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው ማርሻል አርት ነበር። አሁን ግን በተሻለ ነገር ተክቼዋለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የሚከተለው ሐሳብ ስሜቴን ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል፦ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ይጠቅማል፤ ለአምላክ ማደር ግን ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ ሕይወት ተስፋ ስለሚሰጥ ለሁሉም ነገር ይጠቅማል።”—1 ጢሞቴዎስ 4:8

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።