በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ የሆኑት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ የሆኑት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ የሆኑት በሃይማኖታዊ እምነታቸው የተነሳ ይኸውም የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ ሲሉ ነው። በመሆኑም የቅስቀሳ ዘመቻ አናካሂድም፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወይም እጩዎችን አንመርጥም፤ ለምርጫ አንወዳደርም፤ እንዲሁም መንግሥት ለመቀየር በሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ አንካፈልም። እንዲህ ማድረግ የሌለብን ለምን እንደሆነ የሚያሳዩ አጥጋቢ ምክንያቶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተምረናል።

  • የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን፤ ኢየሱስ የፖለቲካ ሥልጣን ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበረም። (ዮሐንስ 6:15) በተጨማሪም የእሱ ተከታዮች “የዓለም ክፍል” መሆን እንደሌለባቸው ያስተማረ ከመሆኑም ሌላ ክርስቲያኖች በፖለቲካ ጉዳዮች ለማንም መወገን እንደሌለባቸው ግልጽ አድርጓል።—ዮሐንስ 17:14, 16፤ 18:36፤ ማርቆስ 12:13-17

  • ከሁሉ ይበልጥ ታማኝነታችንን የምናሳየው ለአምላክ መንግሥት ነው፤ ኢየሱስ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል” ሲል ስለ አምላክ መንግሥት መናገሩ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) ስለ አምላክ መንግሥት መምጣት እንድናውጅ ተልዕኮ የተሰጠን የመንግሥቱ ተወካዮች እንደመሆናችን መጠን የምንኖርበትን አገር ጨምሮ በየትኛውም አገር ባለ የፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ እጃችንን አናስገባም።—2 ቆሮንቶስ 5:20፤ ኤፌሶን 6:20

  • ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ መሆናችን የትኛውም ዓይነት የፖለቲካ አቋም ላላቸው ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች በነፃነት እንድንናገር አስችሎናል። በዓለም ላይ ላሉት ችግሮች መፍትሔ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ያለንን እምነት በንግግራችንም ሆነ በድርጊታችን ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን።—መዝሙር 56:11

  • በመካከላችን የፖለቲካ ክፍፍል ስለሌለ በዓለም ዙሪያ አንድነት ያለው የወንድማማች ማኅበር ሊኖረን ችሏል። (ቆላስይስ 3:14፤ 1 ጴጥሮስ 2:17) ከዚህ በተለየ መልኩ በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ የሚገቡ ሃይማኖቶች በአባሎቻቸው መካከል መከፋፈል እንዲኖር ያደርጋሉ።—1 ቆሮንቶስ 1:10

መንግሥታትን እናከብራለን። በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ባንገባም በምንኖርበት አገር ያለውን መንግሥት ሥልጣን እናከብራለን። ይህም “ነፍስ ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ጋር የሚስማማ ነው። (ሮም 13:1) ሕግ እናከብራለን፤ ግብር እንከፍላለን፤ እንዲሁም መንግሥት የዜጎቹን ኑሮ ለማሻሻል የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ለመደገፍ ፈቃደኞች ነን። መንግሥት ለመገልበጥ በሚደረጉ ሙከራዎች አንሳተፍም፤ ከዚህ ይልቅ “ነገሥታትንና በሥልጣን ላይ ያሉትን ሁሉ በተመለከተ” ጸሎት እንድናደርግ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እንከተላለን፤ በተለይም እነዚህ መንግሥታት የአምልኮ ነፃነትን ሊነካ የሚችል ውሳኔ ለማድረግ በሚነሱበት ጊዜ እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2

ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ሰዎች ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የራሳቸውን ውሳኔ የማድረግ መብታቸውን አንጋፋም። ለምሳሌ ያህል፣ በፖለቲካ ምርጫ ወቅት ረብሻ አናነሳም፤ እንዲሁም መምረጥ የሚፈልጉ ካሉ በእነሱ ውሳኔ አንገባም።

የገለልተኝነት አቋማችን በዚህ ዘመን የመጣ ነገር ነው? አይደለም። ሐዋርያትና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ሌሎች ክርስቲያኖች ከመንግሥት ሥልጣን ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ አቋም ነበራቸው። ቢዮንድ ጉድ ኢንቴንሽንስ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው “የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የመንግሥትን ሥልጣን የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው ቢያውቁም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ መግባት ተገቢ እንደሆነ አያምኑም ነበር።” በተመሳሳይም ኦን ዘ ሮድ ቱ ሲቪላይዜሽን የተባለው መጽሐፍ የጥንቶቹን ክርስቲያኖች በተመለከተ “የፖለቲካ ሥልጣን አይዙም ነበር” ብሏል።

ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ መሆናችን የአገሩን ደኅንነት ስጋት ላይ ይጥላል? በፍጹም። ሰላም ወዳድ ዜጎች ስለሆንን የመንግሥት ባለሥልጣናት ምንም የሚሰጉበት ምክንያት የለም። የዩክሬን ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ በ2001 ያወጣውን አንድ ሪፖርት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህ ሪፖርት ስለ ገለልተኝነት አቋማችን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው ይህ አቋም አንዳንዶችን አያስደስታቸው ይሆናል፤ የይሖዋ ምሥክሮች አምባገነን በሆኑት የናዚና የኮሚኒስት አገዛዞች ክስ እንዲሰነዘርባቸው ያደረገው ዋነኛው ምክንያት ይህ ነው።” የይሖዋ ምሥክሮች ጨቋኝ በነበረው የሶቪየት አገዛዝ ወቅትም ጭምር “ሕግ አክባሪ ዜጎች መሆናቸውን አልተዉም። በመንግሥት እርሻዎችና በፋብሪካዎች ውስጥ በሐቀኝነትና በትጋት ይሠሩ የነበረ ሲሆን የኮሚኒስቱን መንግሥት ስጋት ላይ የሚጥል አንዳች ነገር አላደረጉም።” ሪፖርቱ እንደደመደመው አሁንም ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮች እምነትም ሆነ ሃይማኖታዊ ልማዶች “የየትኛውንም አገር ደኅንነትና አንድነት አደጋ ላይ አይጥሉም።”