በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት የማይካፈሉት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት የማይካፈሉት ለምንድን ነው?

 የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት የማይካፈሉት በሚከተሉት ምክንያቶች ነው፦

  1.   አምላክን ስለሚታዘዙ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ አገልጋዮች “ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ” እንደሚያደርጉና ‘ጦርነትን ከእንግዲህ እንደማይማሩ’ ይገልጻል።—ኢሳይያስ 2:4

  2.   ኢየሱስን ስለሚታዘዙ። ኢየሱስ ሐዋርያው ጴጥሮስን፦ “ሰይፍህን ወደ ቦታው መልስ፤ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ።” (ማቴዎስ 26:52) በዚህ መንገድ ኢየሱስ ተከታዮቹ የጦር መሣሪያ እንደማያነሱ ገልጿል።

     የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በፖለቲካዊ ጉዳዮች ፍጹም ገለልተኛ በመሆን ‘የዓለም ክፍል እንዳይሆኑ’ የተሰጣቸውን ትእዛዝ እንዳከበሩ አሳይተዋል። (ዮሐንስ 17:16) ወታደራዊ እርምጃዎችን አይቃወሙም እንዲሁም በውትድርና ለማገልገል በመረጡ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ አያደርጉም።

  3.   ሰዎችን ስለሚወድዱ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ‘እርስ በርሳቸሁ እንዲዋደዱ’ አዝዟል። (ዮሐንስ 13:34, 35) በዚህ መንገድ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር በመመሥረታቸው አንድም የይሖዋ ምሥክር በወንድሙ ወይም በእህቱ ላይ ፈጽሞ ጦርነት አይከፍትም።—1 ዮሐንስ 3:10-12

  4.   የጥንት ክርስቲያኖችን ምሳሌ ስለሚከተሉ። ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ዋር እንደገለጸው “የቀድሞዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች በጦርነትና በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኞች አልነበሩም።” ምክንያቱም እነዚህ ተግባራት “ኢየሱስ ካስተማረው የፍቅር ሕግና ጠላታቸውን እንዲወዱ ከሰጠው ትእዛዝ ጋር የማይስማሙ እንደሆኑ” ተገንዝበው ነበር። በተመሳሳይም ጀርመናዊ የሃይማኖት ምሑር የሆኑት ፒተር ማይንሆልት ስለ ኢየሱስ የጥንት ደቀ መዛሙርት ሲናገሩ “ክርስቲያን መሆንና ውትድርና አብረው ሊሄዱ የማይችሉ ነገሮች እንደሆኑ ይታሰብ ነበር” ብለዋል።

ለኅብረተሰቡ የምናደርገው አስተዋጽኦ

 የይሖዋ ምሥክሮች ኅብረተሰቡን የሚጠቅም ተግባር የሚያከናውኑ ጥሩ ዜጎች ሲሆኑ የሚኖሩበትን አገር ደኅንነት አደጋ ላይ አይጥሉም። በሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዛት የተነሳ የመንግሥትን ሥልጣን እናከብራለን፦

  •   “ነፍስ ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ።”—ሮም 13:1

  •   “የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር የአምላክ የሆነውን ነገር ደግሞ ለአምላክ መልሳችሁ ስጡ።”—ማቴዎስ 22:21

 በመሆኑም ሕጎችን እንታዘዛለን፣ ግብር እንከፍላለን እንዲሁም የመንግሥት ባለሥልጣናት የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ እንተባበራለን።