የወጣቶች ጥያቄ
የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ደርሻለሁ?
የፍቅር ጓደኝነት ሲባል ምን ማለት ነው?
ከአንዲት ወጣት ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ እየተገናኛችሁ ትጫወታላችሁ። የፍቅር ጓደኝነት ጀምረሃል ማለት ይቻላል?
ደስ የምትልህ አንዲት ወጣት አለች፤ እሷም ለአንተ ልዩ ስሜት አላት። በቀን ውስጥ ብዙ ጊዜ በሞባይል መልእክት ትላላካላችሁ አሊያም በስልክ ታወራላችሁ። የፍቅር ጓደኝነት ጀምረሃል ማለት ይቻላል?
ከጓደኞችህ ጋር ጊዜ ስታሳልፍ ሁልጊዜ ከአንዲት ወጣት ጋር ነጠል ብለህ ታወራለህ። የፍቅር ጓደኝነት ጀምረሃል ማለት ይቻላል?
የመጀመሪያውን ጥያቄ ለመመለስ ብዙም እንደማትቸገር ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ሁለተኛውንና ሦስተኛውን ጥያቄ ለመመለስ አመንትተህ ይሆናል። ለመሆኑ የፍቅር ጓደኝነት ሲባል ምን ማለት ነው?
ለአንዲት ወጣት የፍቅር ስሜት ካለህና እሷም እንደ አንተ የሚሰማት ከሆነ የምትገናኙበት መንገድ ምንም ይሁን ምን በመካከላችሁ መፈላለጉ እስካለ ድረስ የፍቅር ጓደኝነት ጀምራችኋል ሊባል ይችላል።
በመሆኑም ከላይ የቀረቡት የሦስቱም ጥያቄዎች መልስ አዎ የሚል ነው። አንተና አንዲት ወጣት አንዳችሁ ለሌላው የፍቅር ስሜት እንዳላችሁ የምታሳዩና በየጊዜው የምታወሩ ከሆነ፣ የምትገናኙት በስልክም ይሁን በአካል ወይም ደግሞ በግልጽም ይሁን በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ጀምራችኋል ማለት ነው።
የፍቅር ጓደኝነት የሚመሠረትበት ዓላማ ምንድን ነው?
የፍቅር ጓደኝነት የሚመሠረትበት ዓላማ ክብር ያለው መሆን ይኖርበታል፤ ዓላማው አንድ ወንድና አንዲት ሴት በትዳር መጣመር ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን የሚያስችል አጋጣሚ መፍጠር ሊሆን ይገባል።
እርግጥ ነው፣ አንዳንድ እኩዮችህ የፍቅር ጓደኝነት መመሥረትን በቁም ነገር አይመለከቱት ይሆናል። ምናልባትም ምንም የማግባት እቅድ ሳይኖራቸው ተቃራኒ ፆታ ካለው አንድ ግለሰብ ጋር ልዩ ቅርርብ መፍጠር ያስደስታቸው ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶች እንዲህ ዓይነት ጓደኝነት የሚመሠርቱት እንዲሁ ከተቃራኒ ፆታ ጋር አብረው መታየት ስለሚፈልጉ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ተፈላጊ መሆናቸውን ለማሳየት ይሆናል።
ይሁንና እንዲህ ዓይነት ብስለት የጎደለው አመለካከት ያላቸው ሰዎች የሚመሠርቱት የፍቅር ጓደኝነት አብዛኛውን ጊዜ በአጭሩ ይቀጫል። ሄዘር የተባለች አንዲት ወጣት “የፍቅር ጓደኝነት የሚመሠርቱ ብዙ ልጆች በአንድ ወይም በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይለያያሉ” በማለት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “እነዚህ ወጣቶች የፍቅር ጓደኝነትን ሲመሠርቱ ለረጅም ጊዜ እንደሚዘልቅ አያስቡም፤ በመሆኑም እንዲህ ያለው ግንኙነት ለፍቺ እንጂ ለትዳር ሕይወት አያዘጋጃቸውም።”
ከአንዲት ወጣት ጋር የፍቅር ጓደኝነት ስትመሠርት ለአንተ ልዩ ስሜት ሊያድርባት እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብሃል። በመሆኑም የፍቅር ግንኙነት የምትመሠርትበትን ዓላማ በቁም ነገር ልታስብበት ይገባል።—ሉቃስ 6:31
የማግባት እቅድ ሳይኖርህ የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት፣ አዲስ አሻንጉሊት ሲያገኝ ተጫውቶበት ሲሰለቸው እንደሚጥል ልጅ መሆን ነው
እስቲ አስበው፦ አሻንጉሊቱን ሲፈልግ እያነሳ የሚጫወትበትና ሲሰለቸው ደግሞ የሚጥል አንድ ትንሽ ልጅ ወደ አእምሮህ ለማምጣት ሞክር፤ አንድ ሰው፣ ልክ እንደዚህ ትንሽ ልጅ በስሜትህ ቢጫወት ምን ይሰማሃል? ደስ እንደማይልህ የታወቀ ነው፤ አንተም በሌላ ሰው ላይ እንደዚህ አታድርግ! መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለ ፍቅር ሲናገር “ተገቢ ያልሆነ ምግባር አያሳይም” ይላል።—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5
ቼልሲ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የፍቅር ጓደኝነት የሚመሠረተው ደስ የሚል ስሜት ስለሚፈጥር ብቻ እንደሆነ የሚሰማኝ ጊዜ አለ፤ ይሁን እንጂ አንደኛው ወገን ጓደኝነቱን በቁም ነገር እየተመለከተው ሌላኛው እንደ ዋዛ የሚያየው ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት አንደኛውን ወገን እንደሚጎዳው ግልጽ ነው።”
ጠቃሚ ምክር፦ የፍቅር ጓደኝነት ለመጀመርና ጋብቻ ለመመሥረት ዝግጁ መሆን እንድትችል 2 ጴጥሮስ 1:5-7ን ካነበብክ በኋላ ልታዳብረው የሚገባህን አንድ ባሕርይ ምረጥ። ከአንድ ወር በኋላ ስለዚህ ባሕርይ ምን ያህል እንዳወቅክና ይህን ባሕርይ በማዳበር ረገድ ምን ማሻሻያ እንዳደረግህ ራስህን ገምግም።
የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት የምችልበት ዕድሜ ላይ ደርሻለሁ?
ወጣቶች በስንት ዓመታቸው የፍቅር ጓደኝነት ቢጀምሩ ጥሩ ነው ትላለህ?
ይህንኑ ጥያቄ ለወላጆችህ አቅርብላቸው።
አንተ የጻፍከው ዕድሜ ወላጆችህ ከነገሩህ የተለየ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። በእርግጥ የተለየ ላይሆንም ይችላል! ይህ ከሆነ፣ ትክክለኛ ፍላጎታቸውን በደንብ የሚያውቁበት ዕድሜ ላይ እስኪደርሱ ድረስ የፍቅር ጓደኝነት ከመመሥረት በመቆጠብ አስተዋይነት የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ካደረጉት በርካታ ወጣቶች አንዱ ነህ ማለት ነው።
የ17 ዓመቷ ዳንየል እንዲህ ዓይነት ውሳኔ አድርጋለች። እንዲህ ብላለች፦ “ከሁለት ዓመት በፊት የነበረኝን አመለካከት መለስ ብዬ ሳስበው የትዳር ጓደኛዬ እንዲሆን ከምፈልገው ሰው እጠብቀው የነበረው ነገር አሁን ከምፈልገው በጣም የተለየ ነው። በመሠረቱ አሁንም እንኳ እንዲህ ዓይነቱን ውሳኔ ማድረግ እችላለሁ ብዬ በራሴ አልተማመንም። ለተወሰኑ ዓመታት ራሴን ከፈተሽኩ በኋላ የሰከነ አቋም እንዳለኝ እርግጠኛ ስሆን፣ ያን ጊዜ የፍቅር ጓደኝነት ስለ መመሥረት ማሰብ እጀምራለሁ።”
የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት አለመጣደፍ የጥበብ እርምጃ ነው የምንልበት ሌላም ምክንያት አለ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ሰው የፆታ ፍላጎቱና ከተቃራኒ ፆታ ጋር ለመሆን ያለው ምኞት ስለሚያይልበት ጊዜ ሲገልጽ “አፍላ የጉርምስና ዕድሜ” የሚለውን ሐረግ ይጠቀማል። (1 ቆሮንቶስ 7:36) ‘በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ’ ላይ እያለህ ከአንዲት ወጣት ጋር ልዩ ቅርርብ መፍጠርህ የፆታ ስሜትህን ይበልጥ ሊያቀጣጥለውና መጥፎ ድርጊት ወደ መፈጸም ሊመራህ ይችላል።
እርግጥ ለእኩዮችህ ይህ ምንም ማለት ላይሆን ይችላል። አብዛኞቹ፣ የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። አንተ ግን እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ተጽዕኖ እንዳያሳድርብህ ማድረግ ትችላለህ፤ ደግሞም ይኖርብሃል! (ሮም 12:2) መጽሐፍ ቅዱስ ‘የፆታ ብልግና ከመፈጸም እንድትርቅ’ ያሳስብሃል። (1 ቆሮንቶስ 6:18 ኒው ኢንተርናሽናል ቨርዥን) አፍላ የጉርምስና ዕድሜን እስክታልፍ ድረስ የፍቅር ጓደኝነት ከመመሥረት በመቆጠብ ‘ክፉ ነገርን ማስወገድ’ ትችላለህ።—መክብብ 11:10
የፍቅር ጓደኝነት ለመጀመር መቸኮል የሌለብህ ለምንድን ነው?
ዝግጁ ሳትሆን የፍቅር ጓደኝነት እንድትጀምር የሚደረግብህ ጫና በደንብ ያልተማርከውን ትምህርት እንድትፈተን ከመገደድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይህ ምክንያታዊ እንዳልሆነ ግልጽ ነው! ፈተና ላይ የሚቀርቡትን ጥያቄዎች መመለስ እንድትችል ትምህርቱን ለማጥናት ጊዜ ያስፈልግሃል።
የፍቅር ጓደኝነት በመመሥረት ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።
የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት እንደ ዋዛ የሚታይ ነገር አይደለም። በመሆኑም ከአንዲት ወጣት ጋር የፍቅር ጓደኝነት ስለ መጀመር ከማሰብህ በፊት በጣም አስፈላጊ የሆነን አንድ “ትምህርት” ለማጥናት ይኸውም ወዳጅነት መመሥረት የሚቻልበትን መንገድ ለመማር በቂ ጊዜ ያስፈልግሃል።
እንዲህ ካደረግህ ከጊዜ በኋላ፣ የምትሆንህን ወጣት ስታገኝ ጠንካራ ግንኙነት ለመመሥረት የተሻለ አቋም ይኖርሃል። ጥሩ ጋብቻ የሁለት ጥሩ ጓደኛሞች ጥምረት መሆኑን አትዘንጋ።
የፍቅር ጓደኝነት ሳትጀምር መቆየትህ ነፃነትህን እንደሚገድብብህ ማሰብ የለብህም። እንዲያውም ‘የወጣትነትህን ጊዜ አስደሳች’ በሆነ መንገድ ለማሳለፍ የበለጠ ነፃነት ይሰጥሃል። (መክብብ 11:9) ከዚህም በተጨማሪ ጥሩ ባሕርያትን በማዳበርና ከምንም በላይ ደግሞ መንፈሳዊነትህን በማጠናከር ራስህን ለማዘጋጀት የሚያስችል ጊዜ ይኖርሃል።—ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:27
እስከዚያው ድረስ ግን ተቃራኒ ፆታ ካላቸው ወጣቶች ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ትችላለህ። ይህን ለማድረግ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው? ትላልቅ ሰዎች ባሉበት በቡድን ሆኖ (ከወንዶችም ሆነ ከሴቶች ጋር) መጫወት ይቻላል። ታሚ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “እንደዚያ ሲሆን ይበልጥ የሚያስደስት ይመስለኛል። ብዙ ጓደኞች ቢኖሩን የተሻለ ነው።” ሞኒካም በዚህ ሐሳብ ትስማማለች። “በቡድን ሆኖ መጫወት በጣም ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም የተለያየ ባሕርይ ያላቸውን ሰዎች ማወቅ ትችላላችሁ” በማለት ተናግራለች።
በሌላ በኩል ግን ያለዕድሜህ በአንድ ሰው ላይ ብቻ ትኩረት የምታደርግ ከሆነ ራስህን ለአደጋ ታጋልጣለህ። ስለዚህ አትቸኩል። ከዚህ ይልቅ ይህንን ዕድሜህን፣ ወዳጅነት መመሥረትና ዘላቂ እንዲሆን ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለመማር ተጠቀምበት። እንዲህ ካደረግህ አንድ ቀን የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ስትወስን፣ የራስህን ፍላጎትም ሆነ የዕድሜ ልክ የትዳር አጋርህ ከምትሆነው ሴት የምትጠብቃቸውን ባሕርያት በሚገባ ታውቃለህ።