በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ስለሚኖሩ ሰዎች ባሕርይ እና ምግባር ትንቢት ተናግሯል?

መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ስለሚኖሩ ሰዎች ባሕርይ እና ምግባር ትንቢት ተናግሯል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አዎ፤ መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ባሕርያቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ እንደሚመጣ ይናገራል። ይህ መሆኑ ደግሞ በዓለም ዙሪያ የሥነ ምግባር ውድቀት እንዲሰፍን እንዲሁም ማኅበራዊ እሴቶች እንዲጠፉ ያደርጋል። a (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት የሥነ ምግባር ውድቀት የሚታየው በሁሉም ሰዎች ላይ እንዳልሆነም ይገልጻል። ከዚህ ይልቅ ብዙ ሰዎች በአምላክ እርዳታ የሌሎችን መጥፎ ተጽዕኖ ለመቋቋም እንዲሁም አስተሳሰባቸውና ምግባራቸው ከእሱ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እንዲሆን ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ።—ኢሳይያስ 2:2, 3

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ስለሚኖሩ ሰዎች ባሕርይ እና ምግባር ምን ትንቢት ተናግሯል?

 መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን በስፋት ስለሚታዩ የተለያዩ መጥፎ ባሕርያትና ድርጊቶች ይናገራል፤ እነዚህ ነገሮች የሚመነጩት ከራስ ወዳድነት ነው። ሰዎች “ራሳቸውን የማይገዙ፣” “ራሳቸውን የሚወዱ” እንዲሁም “ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:2-4

 ልክ ትንቢቱ እንደሚገልጸው በዘመናችን ያሉ ሰዎች ስለ ራሳቸው ብቻ የሚያስቡ፣ ከራሳቸው ጥቅም ሌላ የማይታያቸው፣ የራሳቸውን ስሜት ብቻ የሚያዳምጡ እንዲሁም ራሳቸውን ለማስደሰት ብቻ የሚጥሩ ናቸው። እንደነዚህ ያሉት ባሕርያት በጣም ከመስፋፋታቸው የተነሳ አንዳንዶች ‘ከራሱ ውጭ የማያውቅ ትውልድ’ እና ‘ሁሉን ነገር ለእኔ የሚል ትውልድ’ የሚሉ አገላለጾችን ሲጠቀሙ እንሰማለን። ብዙ ሰዎች የሚያስቡት ስለ ራሳቸው ብቻ ስለሆነ “ጥሩ ነገር የማይወዱ” ናቸው፤ በሌላ አባባል መልካም ባሕርያትን እንኳ አይወዱም። “የማያመሰግኑ” ስለሆኑ ላላቸው ነገር ወይም ሌሎች ላደረጉላቸው ነገር አድናቆት ማሳየት እንደሚያስፈልግ አይሰማቸውም።—2 ጢሞቴዎስ 3:2, 3

 ከራስ ወዳድነት የሚመነጩ የዘመናችን መለያ የሆኑ ሌሎች ባሕርያትም አሉ፦

  •   ስግብግቦች። ብዙ ሰዎች “ገንዘብ የሚወዱ” ናቸው፤ ስኬታቸውን የሚለኩት በገቢያቸው ወይም በንብረታቸው መጠን ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:2

  •   ኩራተኞች። ብዙዎች “ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች” እና “በኩራት የተወጠሩ” ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:2, 4) እንዲህ ያሉት ሰዎች ስለ ችሎታቸው፣ ስለ ብቃታቸው ወይም ስለ ሀብታቸው ጉራቸውን ይነዛሉ።

  •   ስም አጥፊዎች። “ተሳዳቢዎች” እና “ስም አጥፊዎች” የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:2, 3) እነዚህ ሰዎች፣ ሌሎች ሰዎችን ወይም አምላክን ይሳደባሉ፤ አሊያም ስለ እነሱ ውሸት ያወራሉ።

  •   ግትሮች። ብዙ ሰዎች “ታማኝ ያልሆኑ፣” “ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣” “ከዳተኞች” እና “ግትሮች” ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:2-4) ለመደራደር፣ የጋራ መፍትሔ ለመፈለግ ወይም የገቡትን ቃል ለማክበር ፈቃደኞች አይደሉም።

  •   ዓመፀኞች። በዛሬው ጊዜ ብዙዎች “ጨካኞች” ናቸው። በትንሽ በትልቁ በቁጣ ይገነፍላሉ፤ በዚህም ምክንያት አሰቃቂ ወይም ዘግናኝ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:3

  •   ሕገ ወጦች። ኢየሱስ በዘመናችን “ሕገ ወጥነት እየበዛ” እንደሚሄድ አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:12 የግርጌ ማስታወሻ) በተጨማሪም “ብጥብጥ” ወይም “ረብሻ” እንደሚስፋፋ ተንብዮአል።—ሉቃስ 21:9 የግርጌ ማስታወሻ

  •   ለቤተሰብ ፍቅር የሌላቸው። ሰዎች “ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ” እና “ተፈጥሯዊ [የቤተሰብ] ፍቅር የሌላቸው” በመሆናቸው በቤተሰባቸው አባላት ችላ የሚባሉ ይባስ ብሎም ጥቃት የሚደርስባቸው ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል።—2 ጢሞቴዎስ 3:2, 3

  •   ግብዞች። “ለአምላክ ያደሩ መስለው [የሚታዩ]” ሆኖም አምላክን የማያከብሩ ሰዎች ቁጥራቸው እየበዛ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:5) እነዚህ ሰዎች የአምላክን ፈቃድ ከማድረግ ይልቅ፣ መስማት የሚፈልጉትን የሚነግሯቸውን የሃይማኖት መሪዎች ይከተላሉ።—2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4

 ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ?

 ራስ ወዳድነት መስፋፋቱ ብዙዎችን ለአእምሯዊና ለስሜታዊ ሥቃይ ዳርጓል። (መክብብ 7:7) ለምሳሌ ያህል፣ ገንዘብን የሚወዱ አንዳንድ ሰዎች የሌሎችን ጉልበት ይበዘብዛሉ ወይም ያጭበረብራሉ። ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው ሰዎች በቤተሰባቸው አባላት ላይ ጥቃት ይሰነዝሩ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ጥቃት የደረሰባቸው የቤተሰብ አባላት በመንፈስ ጭንቀት እንዲዋጡ ይባስ ብሎም ራሳቸውን ለማጥፋት እንዲያስቡ ሊያደርግ ይችላል። ክህደት የሚፈጽሙ ሰዎች ደግሞ የክህደታቸው ሰለባ የሆኑትን ሰዎች ለስሜት ቁስል ይዳርጋሉ።

 የአብዛኞቹ ሰዎች ባሕርይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ የመጣው ለምንድን ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎች ባሕርይ እንዲበላሽ ያደረገው ምን እንደሆነ ይናገራል፦

  •   ሰዎች ለአምላክም ሆነ ለሌሎች ያላቸው ፍቅር እየቀነሰ ነው። (ማቴዎስ 24:12) ይህ ደግሞ ራስ ወዳድነት እንዲጨምር አድርጓል።

  •   ሰይጣን ዲያብሎስ ከሰማይ የተባረረ ሲሆን እንቅስቃሴው በምድር አካባቢ ብቻ ተገድቧል። (ራእይ 12:9, 12) ይህ ከሆነ ጊዜ አንስቶ ሰይጣን የሰው ልጆች ይበልጥ ክፉና ራስ ወዳድ እንዲሆኑ ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል።—1 ዮሐንስ 5:19

 የሰዎች ባሕርይ እየተበላሸ ሲሄድ እኛ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

 የአምላክ ቃል “ከእነዚህ [ሰዎች] ራቅ” ይላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:5) እርግጥ ነው፣ ይህ ሲባል ከማኅበረሰቡ ራሳችንን ማግለል ይኖርብናል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ራስ ወዳድ ከሆኑና ፈሪሃ አምላክ ከሌላቸው ሰዎች ጋር የቅርብ ወዳጅነት ላለመመሥረት እንጠነቀቃለን ማለት ነው።—ያዕቆብ 4:4

 የሚበላሸው የሁሉም ሰው ባሕርይ ነው?

 አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ሰዎች ‘እየተፈጸሙ ባሉት አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ እንደሚያዝኑና እንደሚቃትቱ’ አስቀድሞ ተናግሯል። (ሕዝቅኤል 9:4) እነዚህ ሰዎች ራስ ወዳድ ላለመሆን ጥረት ያደርጋሉ፤ እንዲሁም በአምላክ መሥፈርቶች ይመራሉ። አነጋገራቸውና ምግባራቸው ከብዙኃኑ በእጅጉ የተለየ ይሆናል። (ሚልክያስ 3:16, 18) ለምሳሌ ከሁሉም ሰው ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት ያደርጋሉ፤ እንዲሁም በጦርነትና በዓመፅ አይካፈሉም።—ሚክያስ 4:3

 የሰው ዘር ማኅበረሰብ ከመበላሸቱ የተነሳ ሥርዓት አልበኝነት የሚነግሥበት ደረጃ ላይ ይደርስ ይሆን?

 በፍጹም። የሰው ዘር ማኅበረሰብ ሊወጣው የማይችል ቀውስ ውስጥ ይገባል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ የእሱን መሥፈርቶች የማያከብሩ ሰዎችን በቅርቡ ያጠፋል። (መዝሙር 37:38) ከዚያም “አዲስ ምድር” ወይም አዲስ ማኅበረሰብ ይመሠርታል፤ የዋሆች በምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ መዝሙር 37:11, 29) ይህ ተስፋ የሕልም እንጀራ አይደለም። በአሁኑ ጊዜም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ በርካታ ሰዎች አኗኗራቸውን እንዲያስተካክሉና በአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች እንዲመሩ እየረዳቸው ነው።—ኤፌሶን 4:23, 24

a የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችና በዓለም ላይ የሚታየው ሁኔታ የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ እንደሆነ ያረጋግጣሉ፤ ይህ ጊዜ “በዓይነቱ ልዩ የሆነ” ወይም “የሚያስጨንቅ” ዘመን ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1 የ1954 ትርጉም) ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “‘የመጨረሻው ዘመን’ ምልክት ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።