በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ፋሲካ ምንድን ነው?

ፋሲካ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ፋሲካ አምላክ በ1513 ዓ.ዓ. እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ያወጣበትን ጊዜ ለማስታወስ አይሁዳውያን የሚያከብሩት በዓል ነው። አምላክ ይህን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በዓል አቢብ በተባለው ወር (ይህ ወር ከጊዜ በኋላ ኒሳን ተብሎ ተጠርቷል) በ14ኛው ቀን በየዓመቱ እንዲያከብሩ እስራኤላውያንን አዟቸው ነበር።—ዘፀአት 12:42፤ ዘሌዋውያን 23:5

ፋሲካ ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው?

 ፋሲካ የሚለው ቃል የሚያመለክተው አምላክ በግብፅ ምድር ያሉ በኩራትን በሙሉ ለማጥፋት ካመጣው መቅሰፍት እስራኤላውያን እንዲተርፉ ያደረገበትን ጊዜ ነው። (ዘፀአት 12:27፤ 13:15) አምላክ ይህን አስከፊ መዓት በምድሪቱ ላይ ከማምጣቱ በፊት ለእስራኤላውያን አንድ ትዕዛዝ ሰጣቸው፤ የበግ ወይም የፍየል ጠቦት እንዲያርዱና ደሙን በበራቸው መቃን ላይ እንዲረጩ አዘዛቸው። (ዘፀአት 12:21, 22) አምላክ ይህን ምልክት ሲያይ ቤታቸውን ‘አልፎ ይሄዳል’፤ ይህም በኩራታቸው ከጥፋት እንዲተርፉ ያደርጋል።—ዘፀአት 12:7, 13

በጥንት ዘመን ፋሲካ ይከበር የነበረው እንዴት ነው?

 አምላክ የመጀመሪያው ፋሲካ a እንዴት መከበር እንዳለበት ለእስራኤላውያን መመሪያ ሰጥቶ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ የፋሲካ በዓል አንዳንድ ገጽታዎችን እስቲ እንመልከት።

  •   መሥዋዕት፦ እያንዳንዱ ቤተሰብ በአቢብ (ኒሳን) ወር አሥረኛው ቀን ላይ አንድ ዓመት የሞላውን የበግ ወይም የፍየል ጠቦት ይመርጣል፤ ከዚያም በ14ኛው ቀን ላይ ጠቦቱን ያርዱታል። በመጀመሪያው የፋሲካ በዓል ወቅት አይሁዳውያን ያረዱትን ጠቦት ደም በበራቸው መቃኖች እና በጉበኑ ላይ ረጭተው የነበረ ሲሆን ሥጋውንም ጠብሰው በልተዋል።—ዘፀአት 12:3-9

  •   ምግብ፦ እስራኤላውያን በፋሲካ በዓል ዕለት ከበግ ወይም ከፍየል ሥጋ በተጨማሪ፣ ቂጣ እና መራራ ቅጠል ይበሉ ነበር።—ዘፀአት 12:8

  •   የበዓሉ አከባበር፦ እስራኤላውያን ከፋሲካ በኋላ ባሉት ሰባት ቀናት የቂጣ በዓልን ያከብሩ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ እርሾ ያለበት ዳቦ አይበሉም ነበር።—ዘፀአት 12:17-20፤ 2 ዜና መዋዕል 30:21

  •   ትምህርት፦ የፋሲካ በዓል፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ይሖዋ አምላክ ለማስተማር እንዲችሉ ይረዳቸዋል።—ዘፀአት 12:25-27

  •   ጉዞ፦ ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን የፋሲካ በዓልን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዙ ነበር።—ዘዳግም 16:5-7፤ ሉቃስ 2:41

  •   ሌሎች ልማዶች፦ በኢየሱስ ዘመን የፋሲካ በዓል በሚከበርበት ወቅት ወይን መጠጣት እና መዝሙር መዘመር የተለመዱ ነገሮች ነበሩ።—ማቴዎስ 26:19, 30፤ ሉቃስ 22:15-18

ብዙዎች የፋሲካ በዓልን በተመለከተ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

 የተሳሳተ አመለካከት፦ እስራኤላውያን የፋሲካን ምግብ የበሉት ኒሳን 15 ላይ ነው።

 እውነታው፦ አምላክ እስራኤላውያን ጠቦቱን እንዲያርዱ ያዘዘው ኒሳን 14 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ሲሆን ሥጋውን መብላት የነበረባቸውም በዚያው ምሽት ነው። (ዘፀአት 12:6, 8) በእስራኤላውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት፣ አንድ ቀን የሚጀምረው ፀሐይ ስትጠልቅ ሲሆን የሚያበቃው ደግሞ በቀጣዩ ቀን ፀሐይ ስትጠልቅ ነው። (ዘሌዋውያን 23:32) ስለዚህ እስራኤላውያን የፋሲካውን ጠቦት ያረዱት እና የበሉት ኒሳን 14 ሲጀምር ነበር።

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ክርስቲያኖች የፋሲካ በዓልን ማክበር አለባቸው።

 እውነታው፦ ኢየሱስ በኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ፋሲካን ካከበረ በኋላ የጌታ ራት የሚባል አዲስ የመታሰቢያ በዓል አቋቁሟል። (ሉቃስ 22:19, 20፤ 1 ቆሮንቶስ 11:20) የጌታ ራት ‘የፋሲካ በግ ሆኖ የተሰዋው የክርስቶስ’ መታሰቢያ በዓል ስለሆነ የፋሲካ በዓልን የሚተካ ነው። (1 ቆሮንቶስ 5:7) የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሰዎችን ሁሉ ከኃጢአት እና ከሞት ባርነት ነፃ ስለሚያወጣ በፋሲካ በዓል ወቅት ይቀርብ ከነበረው ከየትኛውም መሥዋዕት እጅግ የላቀ ነው።—ማቴዎስ 20:28፤ ዕብራውያን 9:15

a ከጊዜ በኋላ ግን አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ አስፈልጎ ነበር። ለምሳሌ፣ እስራኤላውያን ከግብጽ ለመውጣት በዝግጅት ላይ ስለነበሩ የመጀመሪያውን የፋሲካ በዓል ያከበሩት “በጥድፊያ” ነበር። (ዘፀአት 12:11) ይሁን እንጂ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ በዓሉን በጥድፊያ ማክበር አያስፈልጋቸውም ነበር።