በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ጥምቀት ምንድን ነው?

ጥምቀት ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ጥምቀት፣ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣትን ያመለክታል። * ኢየሱስ ትልቅ ወንዝ ውስጥ የተጠመቀው ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 3:13, 16) በተመሳሳይም ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ለመጠመቅ ሲጠይቅ ከፊልጶስ ጋር “ውኃው ውስጥ” ገብተዋል።—የሐዋርያት ሥራ 8:36-40

የጥምቀት ትርጉም

መጽሐፍ ቅዱስ ጥምቀትን ከመቀበር ጋር ያመሳስለዋል። (ሮም 6:4፤ ቆላስይስ 2:12) አንድ ሰው በውኃ መጠመቁ፣ ለቀድሞው አኗኗሩ መሞቱንና ራሱን ለአምላክ የወሰነ ክርስቲያን በመሆን አዲስ ሕይወት መጀመሩን ያመለክታል። ጥምቀትና ወደ ጥምቀት የሚያመሩት እርምጃዎች፣ በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች ንጹሕ ሕሊና እንዲያገኙ አምላክ ያደረገው ዝግጅት ነው። (1 ጴጥሮስ 3:21) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ መጠመቅ እንዳለባቸው ያስተማረው በዚህ ምክንያት ነው።—ማቴዎስ 28:19, 20

የውኃ ጥምቀት ከኃጢአት ያነጻል?

አያነጻም። መጽሐፍ ቅዱስ ከኃጢአት የሚያነጻን የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ብቻ እንደሆነ ያስተምራል። (ሮም 5:8, 9፤ 1 ዮሐንስ 1:7) ሆኖም አንድ ሰው ከኢየሱስ መሥዋዕት ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለገ በኢየሱስ ማመን እንዲሁም የቀድሞ አኗኗሩን በመቀየር ኢየሱስ ካስተማራቸው ትምህርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ከዚያም መጠመቅ አለበት።—የሐዋርያት ሥራ 2:38፤ 3:19

ክርስትና ማንሳት ምንድን ነው?

“ክርስትና ማንሳት” የሚለው ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ክርስትና ማንሳት፣ አንዳንድ ቤተ ክርስቲያኖች ሕፃናትን “የሚያጠምቁበትን” (በራሳቸው ላይ ውኃ በመርጨት ወይም በማፍሰስ) እና ስም የሚያወጡበትን ሥርዓት ያመለክታል።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕፃናት መጠመቅ እንዳለባቸው ያስተምራል?

አያስተምርም። በክርስትና እምነት ለመጠመቅ ብቁ የሚሆኑት ‘የአምላክን መንግሥት ምሥራች’ ለመረዳትና ለማመን ዕድሜያቸው የደረሰ ሰዎች ናቸው። (የሐዋርያት ሥራ 8:12) ጥምቀት የአምላክን ቃል መስማትን፣ መቀበልንና ንስሐ መግባትን ይጨምራል፤ አንድ ሕፃን ደግሞ እነዚህን ነገሮች ሊያደርግ አይችልም።—የሐዋርያት ሥራ 2:22, 38, 41

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው ክርስቲያን ወላጆች ያሏቸው ትናንሽ ልጆች፣ ወላጆቻቸው በተከተሉት የታማኝነት ጎዳና የተነሳ በአምላክ ዓይን ቅዱስ ወይም ንጹሕ ተደርገው ይቆጠራሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:14) የሕፃናት ጥምቀት ተቀባይነት ያለው ነገር ቢሆን ኖሮ እነዚህ ልጆች በወላጆቻቸው ሥራ እንደ ቅዱስ መቆጠር አያስፈልጋቸውም ነበር። *

ሰዎች የክርስቲያኖችን ጥምቀት በተመለከተ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

የተሳሳተ አመለካከት፦ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በማጥለቅ ፋንታ ግለሰቡ ላይ ውኃ መርጨት ወይም ማፍሰስ ይቻላል።

እውነታው፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የምናገኛቸው ስለ ጥምቀት የሚናገሩ ዘገባዎች በሙሉ የሚናገሩት ውኃ ውስጥ ስለመጥለቅ ነው። ለምሳሌ ደቀ መዝሙሩ ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ሰው ባጠመቀው ጊዜ ‘ሁለቱም ወርደው ውኃ ውስጥ እንደገቡ’ ዘገባው ይናገራል። በኋላም ‘ከውኃው ወጡ።’—የሐዋርያት ሥራ 8:36-39 *

የተሳሳተ አመለካከት፦ መጽሐፍ ቅዱስ በቤት ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ እንደተጠመቁ መናገሩ ሕፃናትም እንደተጠመቁ ይጠቁማል። ለምሳሌ በፊልጵስዩስ ስለነበረው የእስር ቤት ጠባቂ ሲናገር “እሱና መላው ቤተሰቡ . . . ተጠመቁ” ይላል።—የሐዋርያት ሥራ 16:33

እውነታው፦ ስለ እስር ቤቱ ጠባቂ የሚናገረው ዘገባ የተጠመቁት ሰዎች “የይሖዋን ቃል” እንደተረዱና ሁሉም ‘እጅግ እንደተደሰቱ’ ይገልጻል። (የሐዋርያት ሥራ 16:32, 34) ሕፃናት የይሖዋን ቃል ሊረዱ ስለማይችሉ የእስር ቤት ጠባቂው ቤተሰቦች በተጠመቁበት ጊዜ ሕፃናት እንዳልተካተቱ መደምደም እንችላለን።

የተሳሳተ አመለካከት፦ ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት የሚገባው ለልጆች እንደሆነ መናገሩ ሕፃናት መጠመቅ እንዳለባቸው ያሳያል።—ማቴዎስ 19:13-15፤ ማርቆስ 10:13-16

እውነታው፦ ኢየሱስ ይህን ሐሳብ በጠቀሰበት ወቅት ስለ ጥምቀት እየተናገረ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ለአምላክ መንግሥት ብቁ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች እንደ ልጆች ትሑትና ለመማር ፈቃደኞች መሆን እንዳለባቸው መጠቆሙ ነበር።—ማቴዎስ 18:4፤ ሉቃስ 18:16, 17

^ አን.3 “ጥምቀት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ማጥለቅ” የሚል ፍቺ ካለው ቃል የመጣ ነው። ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 529 ተመልከት።

^ አን.12 ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ “በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ ሕፃናት ጥምቀት የሚናገር ምንም ዘገባ የለም” ይላል። አክሎም ይህ ልማድ “ሰዎች ስለ ጥምቀት ካላቸው የተሳሳተና የተጋነነ አመለካከት” ማለትም ጥምቀት በራሱ ከኃጢአት እንደሚያነጻ ካላቸው እምነት የመነጨ እንደሆነ ይናገራል።—ጥራዝ 1 ገጽ 416-417

^ አን.15 ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ በተባለው መጽሐፍ ላይ “ጥምቀት (በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ)” በሚለው ርዕስ ሥር “በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጥምቀት የሚከናወነው ውኃ ውስጥ በማጥለቅ እንደሆነ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ” የሚል ሐሳብ ሰፍሯል።—ጥራዝ 2 ገጽ 59