በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ጠፍጣፋ እንደሆነች ያስተምራል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ጠፍጣፋ እንደሆነች ያስተምራል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ጠፍጣፋ እንደሆነች አያስተምርም። a መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ ማስተማሪያ መጽሐፍ ባይሆንም በሳይንስ ከተረጋገጡ እውነታዎች ጋር የሚጋጭ አንድም ሐሳብ አልያዘም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ሐሳቦች “ምንጊዜም አስተማማኝ ናቸው።”—መዝሙር 111:8

 መጽሐፍ ቅዱስ ‘አራቱ የምድር ማዕዘኖች’ ሲል ምን ማለቱ ነው?

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ‘አራቱ የምድር ማዕዘኖች’ እንዲሁም ‘የምድር ዳርቻ’ የሚሉት አገላለጾች ቃል በቃል ምድር አራት ማዕዘን እንደሆነች አሊያም ዳርቻ እንዳላት የሚያሳዩ አገላለጾች አይደሉም። (ኢሳይያስ 11:12፤ ኢዮብ 37:3) ከዚህ ይልቅ መላውን ምድር ለማመልከት የሚሠራባቸው ምሳሌያዊ አገላለጾች እንደሆኑ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ አራቱን የምድር አቅጣጫዎችም በተመሳሳይ መንገድ ይጠቀምባቸዋል።—ሉቃስ 13:29

 “ማዕዘኖች” ወይም “ዳርቻ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ አገላለጽ “ክንፎች” በሚለው ቃል ላይ የተመሠረተ ምሳሌያዊ አነጋገር ሳይሆን አይቀርም። ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ኢንሳይክሎፒድያ እንደገለጸው “የወፍ ክንፍ ለጫጩቶቿ እንደ መከለያ ሆኖ የሚያገለግል ከመሆኑ አንጻር [ይህ የዕብራይስጥ አገላለጽ] ማንኛውንም የተዘረጋ ነገር ጫፍ ለማመልከት ተሠርቶበታል።” አክሎም ይኸው የማመሣከሪያ ጽሑፍ፣ የዕብራይስጡ ቃል በኢዮብ 37:3 እና በኢሳይያስ 11:12 ላይ ባለው አገባቡ “በምድር ላይ ያለውን መሬት ዳርቻ፣ ወሰን ወይም ጫፍ ያመለክታል” ይላል። b

 ዲያብሎስ ለኢየሱስ ያቀረበውን ፈተና በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል?

 ዲያብሎስ ኢየሱስን ለመፈተን “በጣም ረጅም ወደሆነ ተራራ ወስዶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየው።” (ማቴዎስ 4:8) አንዳንዶች ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ፣ ከአንድ ቦታ ላይ ሆኖ መላውን ዓለም መመልከት እንደሚቻል ስለሚገልጽ ምድር ጠፍጣፋ እንደሆነች ይጠቁማል ሲሉ ይናገራሉ። ሆኖም በዚህ ዘገባ ላይ የተገለጸው ‘በጣም ረጅም የሆነ ተራራ’ ቃል በቃል ያለን አንድ ቦታ የሚያመለክት ሳይሆን ዘይቤያዊ አነጋገር ይመስላል። ይህ መደምደሚያ አሳማኝ የሆነበትን ምክንያት ተመልከት፦

  •   የዓለምን መንግሥታት ሁሉ ለማየት የሚያስችል ተራራ በምድር ላይ የለም።

  •   ዲያብሎስ ለኢየሱስ ያሳየው የዓለምን መንግሥታት ብቻ ሳይሆን “ክብራቸውን” ጭምር ነው። እንዲህ ያለውን ዝርዝር ነገር ከርቀት ማየት እንደማይቻል የታወቀ ነው፤ በመሆኑም ዲያብሎስ እነዚህን ነገሮች ለኢየሱስ ያሳየው በራእይ አማካኝነት ሳይሆን አይቀርም። ይህም፣ አንድ ሰው የተለያዩ የምድር ክፍሎችን በፕሮጀክተር አማካኝነት ስክሪን ላይ ከሚያሳይበት መንገድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል።

  •   በሉቃስ 4:5 ላይ በሚገኘው ተመሳሳይ ዘገባ ላይ ዲያብሎስ ለኢየሱስ “የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው” ይላል፤ የሰው ዓይን ደግሞ በዚህ ፍጥነት ይህን ሁሉ ነገር ማየት አይችልም። ይህም ዲያብሎስ ለኢየሱስ ፈተናውን ያቀረበው የዓለምን መንግሥታት ቃል በቃል በማሳየት ሳይሆን በሌላ ዘዴ ተጠቅሞ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል።

a መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ክብ ከሆነችው ምድር በላይ ይኖራል” ሲል ይናገራል። (ኢሳይያስ 40:22) አንዳንድ የማመሣከሪያ ጽሑፎች እዚህ ጥቅስ ላይ “ክብ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ድቡልቡል የሚል ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል ይገልጻሉ፤ እርግጥ በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት ሁሉም ምሁራን አይደሉም። ያም ሆነ ይህ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ጠፍጣፋ እንደሆነች የሚገልጸውን ሐሳብ አይደግፍም።

b ተሻሽሎ የቀረበ፣ ጥራዝ 2 ገጽ 4