በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ገንዘብ የክፋት ሁሉ ሥር ነው?

ገንዘብ የክፋት ሁሉ ሥር ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ገንዘብ መጥፎ ነገር እንደሆነ አይገልጽም፤ ገንዘብ የክፉ ነገሮች ሁሉ መንስኤ እንደሆነም አይናገርም። ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደተወሰደ የሚነገርለት “ገንዘብ የክፋት ሁሉ ሥር ነው” የሚለው የተለመደ አባባል የጥቅሱን የተሟላ ሐሳብ ያልያዘና የተሳሳተ መልእክት የሚያስተላልፍ ነው። ትክክለኛው የጥቅሱ ሐሳብ “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው” a የሚል ነው።—1 ጢሞቴዎስ 6:10 የ1954 ትርጉም፤ ጎላ አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።

 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገንዘብ ምን ያስተምራል?

 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ገንዘብን በጥበብ እስከተጠቀምንበት ድረስ ሊጠቅመን እንደሚችል እንዲያውም “ጥበቃ” እንደሚያስገኝልን ይገልጻል። (መክብብ 7:12) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ገንዘብን ጨምሮ ያላቸውን ነገር ለሌሎች በልግስና የሚሰጡ ሰዎችን ያመሰግናል።—ምሳሌ 11:25

 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ፣ በሕይወታችን ውስጥ ለገንዘብ ትልቅ ቦታ እንዳንሰጥ ያስጠነቅቃል። “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ” ይላል። (ዕብራውያን 13:5) ይህ ጥቅስ ለገንዘብ ከተገቢው ያለፈ ቦታ እንዳንሰጥና ሀብት በማሳደድ ላይ ያተኮረ ሕይወት እንዳንመራ ያሳስበናል። እንደ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ያሉ መሠረታዊ ነገሮችን በማግኘት ረክተን መኖር ይገባናል።—1 ጢሞቴዎስ 6:8

 መጽሐፍ ቅዱስ የገንዘብ ፍቅርን በተመለከተ የሚያስጠነቅቀን ለምንድን ነው?

 ስግብግብ ሰዎች የዘላለም ሕይወት አያገኙም። (ኤፌሶን 5:5) ለዚህ አንዱ ምክንያት፣ ስግብግብነት የጣዖት አምልኮ መሆኑ ነው። (ቆላስይስ 3:5) ሁለተኛ፣ ስግብግብ ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት ሲሉ ብዙውን ጊዜ መልካም የሥነ ምግባር መመሪያዎችን ይጥሳሉ። ምሳሌ 28:20 “ሀብት ለማግኘት የሚጣደፍ [ሰው] ንጽሕናውን ማጉደፉ አይቀርም” ይላል። እንዲህ ያለ ሰው አስፈራርቶ ገንዘብ እንደ መቀበል፣ ዝርፊያ፣ ማጭበርበር፣ አፈና ወይም ነፍስ ግድያ ያሉ ወንጀሎችን ለመፈጸም ሊፈተን ይችላል።

 አንድ ሰው በገንዘብ ፍቅር የተነሳ መጥፎ ድርጊት ባይፈጽምም እንኳ ሌሎች ጉዳቶች ሊደርሱበት ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ ግን ፈተናና ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ፤ እንዲሁም . . . ከንቱና ጎጂ በሆኑ ብዙ ምኞቶች ይያዛሉ” ይላል።—1 ጢሞቴዎስ 6:9

 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገንዘብ የሚሰጠው ምክር ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

 ለገንዘብ ስንል ሥነ ምግባራዊም ሆነ መንፈሳዊ እሴቶቻችንን የማንጥስ ከሆነ ለራሳችን አክብሮት ይኖረናል፤ የአምላክን ሞገስና ድጋፍም እናገኛለን። አምላክ፣ እሱን ለማስደሰት ከልቡ የሚጥርን ሰው በተመለከተ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት ቃል ገብቷል። (ዕብራውያን 13:5, 6) በተጨማሪም “ታማኝ ሰው ብዙ በረከት ያገኛል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷል።—ምሳሌ 28:20

a ጥቅሱ “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነው” ተብሎም ተተርጉሟል።