በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ዲያብሎስ የሚኖረው የት ነው?

ዲያብሎስ የሚኖረው የት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ዲያብሎስ መንፈሳዊ ፍጡር እንደመሆኑ መጠን የሚኖረው በዓይን በማይታይ መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ነው። ያም ቢሆን ይህ ቦታ፣ በዚህ ርዕስ ላይ ባለው ሥዕል ላይ እንደሚታየው ያለ ይኸውም ሰይጣን ክፉዎችን የሚያሠቃይበት እሳታማ ሲኦል አይደለም።

‘በሰማይ ጦርነት ተነሳ’

 ለተወሰነ ጊዜ ሰይጣን ዲያብሎስ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ እንደፈለገ ይንቀሳቀስ ነበር፤ ለምሳሌ ከታማኝ መላእክት ጋር በአምላክ ፊት መቆም ይችል ነበር። (ኢዮብ 1:6) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ‘በሰማይ ጦርነት እንደሚነሳ’ እንዲሁም ሰይጣን ከሰማይ “ወደ ምድር [እንደሚወረወር]” ትንቢት ተናግሯል። (ራእይ 12:7-9) የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠርም ሆነ በዓለም ውስጥ የተከናወኑት ነገሮች ይህ ጦርነት እንደተካሄደ ያረጋግጣሉ። በአሁኑ ጊዜ ዲያብሎስ በምድር አካባቢ ብቻ ተወስኖ እንዲኖር ተደርጓል።

 ታዲያ ይህ ማለት ዲያብሎስ የሚኖረው በምድር ላይ ባለ አንድ የተወሰነ ቦታ ላይ ነው? ለምሳሌ ያህል፣ ጴርጋሞን የተባለው ጥንታዊ ከተማ “የሰይጣን ዙፋን [ያለበት]” እንዲሁም ‘ሰይጣን ያለበት’ ከተማ እንደሆነ ተገልጿል። (ራእይ 2:13) በእርግጥ፣ እነዚህ አገላለጾች በዚህ ከተማ ውስጥ የሰይጣን አምልኮ እንደተስፋፋ የሚያሳዩ መሆን አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዲያብሎስ “የዓለምን መንግሥታት ሁሉ” እንደሚገዛ ይናገራል፤ ከዚህ አንጻር ዲያብሎስ የሚኖረው በምድር ላይ ባለ አንድ የተወሰነ ቦታ ላይ ሳይሆን እንቅስቃሴው በምድር አካባቢ ብቻ እንደተገደበ መደምደም እንችላለን።​—ሉቃስ 4:5, 6