በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ዲያብሎስ ሰዎችን መቆጣጠር ይችላል?

ዲያብሎስ ሰዎችን መቆጣጠር ይችላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ዲያብሎስና አጋንንት በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ “መላው ዓለም . . . በክፉው ኃይል ሥር ነው” የሚለው ለዚህ ነው። (1 ዮሐንስ 5:19) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዲያብሎስ በሰዎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች ይገልጻል።

  •   ማታለያ። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች “የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች መቋቋም” እንዳለባቸው ይናገራል። (ኤፌሶን 6:11) ከሚጠቀምባቸው መሠሪ ዘዴዎች መካከል አንዱ የእሱ ወኪሎች የአምላክ አገልጋዮች እንደሆኑ ሰዎችን ማሳመን ነው።​—2 ቆሮንቶስ 11:13-15

  •   መናፍስታዊ ሥራዎች። ዲያብሎስ ሰዎችን ለማታለል መናፍስት ጠሪዎችን፣ ጠንቋዮችን፣ ሟርተኞችን፣ ወይም ኮከብ ቆጣሪዎችን ይጠቀማል። (ዘዳግም 18:10-12) ዕፆችን መውሰድ፣ ሂፕኖቲዝም እንዲሁም ለማሰላሰል ይረዳሉ በሚባሉ ዘዴዎች አማካኝነት አእምሮ ባዶ እንዲሆን ማድረግ ሰዎች በአጋንንት ቁጥጥር ሥር እንዲወድቁ ያደርጋሉ።​—ሉቃስ 11:24-26

  •   የሐሰት ሃይማኖት። የሐሰት ትምህርቶችን የሚያስተምሩ ሃይማኖቶች ሰዎችን የሚያታልሉ ከመሆኑም በላይ ሰዎች አምላክን እንዳይታዘዙ ያደርጋሉ። (1 ቆሮንቶስ 10:20) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉ የሐሰት እምነቶችን “የአጋንንት ትምህርቶች” በማለት ይጠራቸዋል።​—1 ጢሞቴዎስ 4:1

  •   ሰዎችን መያዝ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ በክፉ መናፍስት ስለተያዙ ሰዎች የሚናገሩ ዘገባዎች ይገኛሉ። በአጋንንት የተያዙ ሰዎች ዓይናቸው የታወረበት፣ መናገር የተሳናቸው አልፎ ተርፎም ራሳቸው ላይ ጉዳት ያደረሱበት ጊዜ አለ።​—ማቴዎስ 12:22፤ ማርቆስ 5:2-5

የዲያብሎስን ተጽዕኖ መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ዲያብሎስ በተሳካ መንገድ መቃወም የምንችልባቸውን መንገዶች ስለሚጠቁመን የአጋንንትን ተጽዕኖ እየፈራን መኖር የለብንም። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፦

  •   የዲያብሎስን ‘ዕቅድ ለማወቅ’ ከፈለግን የሚጠቀምባቸውን መንገዶች ለይተን ማወቅ ይኖርብናል።​—2 ቆሮንቶስ 2:11

  •   ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እውቀት መቅሰም እንዲሁ የተማርከውን ነገር በሥራ ላይ ማዋል ይኖርብሃል። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሥራ ላይ ማዋል በዲያብሎስ ተጽዕኖ ሥር እንዳትወድቅ ይጠብቅሃል።​—ኤፌሶን 6:11-18

  •   ከአጋንንት ጋር የተያያዙ ነገሮችን በሙሉ አስወግድ። (የሐዋርያት ሥራ 19:19) ይህም መናፍስታዊ ድርጊቶችን የሚያበረታቱ ሙዚቃዎችን፣ መጻሕፍትን፣ መጽሔቶችን፣ ፖስተሮችንና ቪዲዮዎችን ይጨምራል።