መጽሐፍ ቅዱስ ደስተኛ ቤተሰብ እንዲኖረኝ ሊረዳኝ ይችላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ደስተኛ ቤተሰብ እንዲኖረኝ ሊረዳኝ ይችላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 እንዴታ! በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በቤተሰብ ሕይወታቸው ደስተኛ እንዲሆኑ የረዷቸው ጥበብ ያዘሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ከዚህ በታች ቀርበዋል፦

  1.   ጋብቻችሁን ሕጋዊ አድርጉ። ሕጋዊ በሆነ መንገድ የተመሠረተ ጋብቻ ዘላለማዊ ጥምረት በመሆኑ ለደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት መሠረት ነው።​—ማቴዎስ 19:4-6

  2.   ፍቅርና አክብሮት አሳዩ። ይህም ሌሎች እናንተን እንዲይዟችሁ በምትፈልጉት መንገድ የትዳር ጓደኛችሁን መያዝን ይጨምራል።​—ማቴዎስ 7:12፤ ኤፌሶን 5:25, 33

  3.   ሻካራ ቃላትን አስወግዱ። የትዳር ጓደኛችሁ የሚጎዳ ነገር ቢናገር ወይም ቢያደርግ እንኳ እናንተ በደግነት ተናገሩ። (ኤፌሶን 4:31, 32) መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 15:1 ላይ “የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቍጣን ይጭራል” ይላል።

  4.   አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ሁኑ። የፍቅር ወይም የፆታ ስሜት ልታሳዩ የሚገባው ለትዳር ጓደኛችሁ ብቻ መሆን አለበት። (ማቴዎስ 5:28) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፣ መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን።”​—ዕብራውያን 13:4

  5.   ልጆቻችሁን በፍቅር አሠልጥኑ። በጣም ጥብቅ ወይም በጣም ልል አትሁኑ።​—ምሳሌ 29:15፤ ቆላስይስ 3:21