በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የዲያብሎስ መልክ ምን ዓይነት ነው?

የዲያብሎስ መልክ ምን ዓይነት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ዲያብሎስ መንፈሳዊ ፍጡር ነው፤ ስለዚህ በዓይን ሊታይ የሚችል አካል የለውም።—ኤፌሶን 6:11, 12

 ብዙ ሠዓሊዎች ዲያብሎስን ቀንድና ጅራት ያለው እንዲሁም በእጁ መንሽ የያዘ ፍየል መሰል ፍጡር አድርገው ይሥሉታል። ዲያብሎስን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲህ አስመስለው የሣሉት በመካከለኛው መቶ ዘመን የኖሩ ሠዓሊዎች እንደሆኑ አንዳንዶች ያምናሉ፤ በእነዚህ ሠዓሊዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩት ደግሞ የጥንት አፈ ታሪኮች እንደሆኑ ይገመታል።

 መጽሐፍ ቅዱስ ዲያብሎስን የሚገልጸው እንዴት ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዲያብሎስ ሲናገር የተለያዩ አገላለጾችን ይጠቀማል። እነዚህ አገላለጾች የዲያብሎስን መልክ ሳይሆን ማንነቱን ለማወቅ ይረዱናል። ከእነዚህ አገላለጾች መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦

  •   የብርሃን መልአክ። ሰዎችን የሚጠቅም መልካም ነገር እንዳለው ለማስመሰል ይሞክራል፤ ይህን የሚያደርገው ሰዎች የአምላክን ሳይሆን የእሱን ትምህርቶች እንዲከተሉ ለማድረግ ነው።—2 ቆሮንቶስ 11:14

  •   የሚያገሳ አንበሳ። በአምላክ አገልጋዮች ላይ ከባድ ጥቃት ይሰነዝራል።—1 ጴጥሮስ 5:8

  •   ታላቅ ዘንዶ። አስፈሪ፣ ኃይለኛና አጥፊ ነው።—ራእይ 12:9