በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የአምላክ ቃል ማን ወይም ምንድን ነው?

የአምላክ ቃል ማን ወይም ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ‘የአምላክ ቃል’ የሚለው አገላለጽ አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው ከአምላክ የመጣን አንድ መልእክት ወይም እንዲህ ያሉ መልእክቶች ስብስብን ነው። (ሉቃስ 11:28) አንዳንድ ቦታዎች ላይ “የአምላክ ቃል” ወይም “ቃል” የሚለው አጠራር በማዕረግነት ተሠርቶበታል።—ራእይ 19:13፤ ዮሐንስ 1:14

 ከአምላክ የመጣ መልእክት። በርካታ ነቢያት የሚናገሩት መልእክት የአምላክ ቃል እንደሆነ ይናገሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኤርምያስ ትንቢታዊ መልእክቶቹን ከመናገሩ በፊት “የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ” በማለት ይናገር ነበር። (ኤርምያስ 1:4, 11, 13፤ 2:1) ነቢዩ ሳሙኤልም አምላክ ንጉሥ አድርጎ እንደመረጠው ለሳኦል ከመናገሩ በፊት “የአምላክን ቃል እንዳሰማህ እዚሁ ቁም” ብሎት ነበር።—1 ሳሙኤል 9:27

 ማዕረግ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ቃል” የሚለው መጠሪያ ኢየሱስ በሰማይ መንፈሳዊ አካል በነበረበት ጊዜም ሆነ በምድር ላይ ሰው በነበረበት ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያመለክት የማዕረግ ስም ሆኖ አገልግሏል። እንዲህ ብሎ ለመደምደም የሚያስችሉ አንዳንድ ምክንያቶች እንመልከት፦

  •   ቃል ሌሎች ፍጥረታት ከመፈጠራቸው በፊት ይኖር ነበር።“በመጀመሪያ ቃል ነበረ . . . እሱም በመጀመሪያ ከአምላክ ጋር ነበር።” (ዮሐንስ 1:1, 2) ኢየሱስ “የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው . . . እሱ ከሌሎች ነገሮች ሁሉ በፊት ነው።”—ቆላስይስ 1:13-15, 17

  •   ቃል ሰው ሆኖ ወደ ምድር መጥቷል። “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም ኖረ።” (ዮሐንስ 1:14) ክርስቶስ ኢየሱስ “ራሱን ባዶ በማድረግ የባሪያን መልክ ያዘ፤ ደግሞም ሰው ሆነ።”—ፊልጵስዩስ 2:5-7

  •   ቃል የአምላክ ልጅ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ ከላይ እንደተጠቀሰው ‘ቃል ሥጋ እንደሆነ’ ከተናገረ በኋላ በመቀጠል እንዲህ ብሏል፦ “አንድያ ልጅ ከአባቱ እንደሚያገኘው ክብር ያለ ክብሩን አየን።” (ዮሐንስ 1:14) ዮሐንስ “ኢየሱስ የአምላክ ልጅ” እንደሆነም ጽፏል።—1 ዮሐንስ 4:15

  •   ቃል የአምላክ ዓይነት ባሕርያት አሉት። ‘ቃል አምላክ ነበር’ ወይም ‘መለኮት ነበር።’ (ዮሐንስ 1:1አን አሜሪካን ትራንስሌሽን) ኢየሱስ “የአምላክ ክብር ነጸብራቅና የማንነቱ ትክክለኛ አምሳያ ነው።”—ዕብራውያን 1:2, 3

  •   ቃል ንጉሥ ሆኖ ይገዛል። መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በራሱ ላይ “ብዙ ዘውዶች” እንዳሉት ይናገራል። (ራእይ 19:12, 13) ቃል “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” ተብሎም ተጠርቷል። (ራእይ 19:16) ኢየሱስ “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” ተብሏል።—1 ጢሞቴዎስ 6:14, 15

  •   ቃል የአምላክ ቃል አቀባይ ሆኖ ያገለግላል። “ቃል” የሚለው የማዕረግ ስም አምላክ መረጃዎችንና መመሪያዎችን ለማስተላለፍ “ቃል” የተባለውን አካል እንደሚጠቀም ያመለክታል። ኢየሱስ ይህን ኃላፊነት እንደተወጣ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ምን እንደምልና ምን እንደምናገር ያዘዘኝ የላከኝ አብ ራሱ ነው። . . . ስለዚህ ምንጊዜም የምናገረው ልክ አባቴ በነገረኝ መሠረት ነው።”—ዮሐንስ 12:49, 50