በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አምላክ ስንት ስሞች አሉት?

አምላክ ስንት ስሞች አሉት?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 የአምላክ የተጸውኦ ስም አንድ ብቻ ነው። ስሙ በዕብራይስጥ יהוה ተብሎ የሚጻፍ ሲሆን በአማርኛ አብዛኛውን ጊዜ “ይሖዋ” ተብሎ ይጠራል። a አምላክ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት “እኔ ይሖዋ ነኝ። ስሜ ይህ ነው” በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 42:8) ይህ ስም በእጅ በተገለበጡ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ላይ 7,000 ጊዜ ያህል ይገኛል፤ የዚህን ያህል በብዛት የሚገኝ የአምላክ የማዕረግ ስም ወይም ሌላ ስም የለም። b

ይሖዋ ሌሎች ስሞች አሉት?

 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን የሚጠራው በአንድ የተጸውኦ ስም ብቻ ቢሆንም አምላክን ለመግለጽ በርካታ የማዕረግ ስሞችን ይጠቀማል። ከዚህ በታች ያለው ዝርዝር ከእነዚህ የማዕረግ ስሞች አንዳንዶቹን እንዲሁም የማዕረግ ስሞቹ ስለ አምላክ ባሕርይ ወይም ማንነት ምን እንደሚያስተምሩን ይገልጻል።

የማዕረግ ስም

የሚገኝበት ጥቅስ

ትርጉም

አላህ

(የለም)

“አላህ” አረብኛ ቃል ሲሆን የተጸውኦ ስም አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ “አምላክ” የሚል ትርጉም ያለው የማዕረግ ስም ነው። በአረብኛና በሌሎች ቋንቋዎች በተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ “አላህ” የሚለው መጠሪያ ይገኛል።

ሁሉን ቻይ

ዘፍጥረት 17:1

ገደብ የለሽ ኃይል አለው። “ሁሉን ቻይ አምላክ” ተብሎ የተተረጎመው ኤልሻዳይ የሚለው የዕብራይስጥ አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰባት ጊዜ ይገኛል።

አልፋና ኦሜጋ

ራእይ 1:8፤ 21:6፤ 22:13

“የመጀመሪያውና የመጨረሻው” ማለት ሲሆን ከይሖዋ በፊትም ሆነ በኋላ ሌላ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሌለ ያመለክታል። (ኢሳይያስ 43:10) አልፋ እና ኦሜጋ የግሪክኛ ቋንቋ የመጀመሪያና የመጨረሻ ፊደላት ናቸው።

ከዘመናት በፊት የነበረው

ዳንኤል 7:9, 13, 22

መጀመሪያ የለውም፤ የትኛውም ነገር ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በፊት እሱ ነበር።—መዝሙር 90:2

ፈጣሪ

ኢሳይያስ 40:28

ሁሉንም ነገር ወደ ሕልውና ያመጣው እሱ ነው።

አባት

ማቴዎስ 6:9

ሕይወት ሰጪ።

አምላክ

ዘፍጥረት 1:1

ሊመለክ የሚገባው፤ ኃያል። ኤሎሂም የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ብዙ ቁጥር ነው፤ ይህም የይሖዋን ግርማና ክብር ያጎላል።

የአማልክት አምላክ

ዘዳግም 10:17

አንዳንዶች ከሚያመልኳቸው ‘ከንቱ የሆኑ አማልክት’ በተለየ እሱ ታላቅ አምላክ ነው።—ኢሳይያስ 2:8

ታላቅ አስተማሪ

ኢሳይያስ 30:20, 21

ጠቃሚ ትምህርትና መመሪያ ይሰጣል።—ኢሳይያስ 48:17, 18

ታላቅ ሠሪ

መዝሙር 149:2

ሁሉንም ነገር ወደ ሕልውና ያመጣው እሱ ነው።—ራእይ 4:11

ደስተኛ አምላክ

1 ጢሞቴዎስ 1:11

ሁልጊዜ ደስተኛ የሆነና ሐሴት የሚያደርግ አምላክ።—መዝሙር 104:31

ጸሎት ሰሚ

መዝሙር 65:2

በእምነት የሚቀርብለትን ጸሎት በሙሉ ይሰማል።

እኔ ነኝ

ዘፀአት 3:14 የ1980 ትርጉም

ዓላማውን ለመፈጸም ሲል መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሆናል። ይህ ሐረግ “መሆን የምሻውን እሆናለሁ” ወይም “መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ” ተብሎም ተተርጉሟል። (በጆሴፍ ብርያንት ሮዘርሃም የተዘጋጀው ዚ ኢምፋሳይዝድ ባይብል፤ አዲስ ዓለም ትርጉም) ይህ አገላለጽ በቀጣዩ ቁጥር ላይ የሚገኘውን ይሖዋ የሚለውን ስም ትርጉም ለመገንዘብ ይረዳናል።—ዘፀአት 3:15

ቀናተኛ

ዘፀአት 34:14 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

በአምልኮ ረገድ ተቀናቃኞቹን አይታገሥም። ይህ ቃል “እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ” ተብሎም ተተርጉሟል።—አዲስ ዓለም ትርጉም

የዘላለም ንጉሥ

ራእይ 15:3

አገዛዙ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ የለውም።

ጌታ

መዝሙር 135:5

ባለቤት ወይም አለቃ ማለት ነው፤ በዕብራይስጥ አዶን እና አዶኒም ይባላል።

ጌታ ፀባዖት

ሮም 9:29 የ1954 ትርጉም

የመላእክት ሠራዊት አዛዥ። “ጌታ ፀባዖት” የሚለው የማዕረግ ስም “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል።—ሮም 9:29 አዲስ ዓለም ትርጉም

ልዑል

መዝሙር 47:2

ከሁሉም የበላይ ነው።

እጅግ ቅዱስ

ምሳሌ 9:10

ከማንም ይበልጥ ቅዱስ (በሥነ ምግባር ንጹሕ) ነው።

ሸክላ ሠሪ

ኢሳይያስ 64:8

ሸክላ ሠሪ በሸክላው ላይ ሥልጣን እንዳለው ሁሉ እሱም በሰዎችና በብሔራት ላይ ሥልጣን አለው።—ሮም 9:20, 21

የሚቤዥ

ኢሳይያስ 41:14

በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ዋጅቷል።—ዮሐንስ 3:16

ዓለት

መዝሙር 18:2, 46

አስተማማኝ መጠጊያና መሸሸጊያ።

አዳኝ

ኢሳይያስ 45:21

ከአደጋ ወይም ከጥፋት የሚታደግ።

እረኛ

መዝሙር 23:1

አገልጋዮቹን የሚንከባከብ።

ሉዓላዊው ጌታ

ዘፍጥረት 15:2

የሁሉም የበላይ፤ በዕብራይስጥ አዶናይ ይባላል።

በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱ የቦታ ስሞች

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ የቦታ ስሞች የአምላክን የተጸውኦ ስም ይዘዋል፤ ሆኖም እነዚህ ስሞች የአምላክ ስም አይደሉም።

የቦታ ስም

የሚገኝበት ጥቅስ

ትርጉም

ይሖዋ ይርኤ

ዘፍጥረት 22:13, 14

“ይሖዋ ያቀርባል።”

ይሖዋ ንሲ

ዘፀአት 17:15

“ይሖዋ አርማዬ ነው።” የይሖዋ ሕዝቦች ጥበቃና እርዳታ ለማግኘት ወደ እሱ ይመጣሉ።—ዘፀአት 17:13-16

ይሖዋ ሻሎም

መሳፍንት 6:23, 24

“ይሖዋ ሰላም ነው።”

የአምላክን ስም ማወቅና ስሙን መጠቀም ያለብን ለምንድን ነው?

  • አምላክ “ይሖዋ” የተባለው ስሙ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ቦታዎች እንዲጠቀስ ማድረጉ ለስሙ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ ያሳያል።—ሚልክያስ 1:11

  • የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ የአምላክ ስም ትልቅ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ በተደጋጋሚ ገልጿል። ለምሳሌ “ስምህ ይቀደስ” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል።—ማቴዎስ 6:9፤ ዮሐንስ 17:6

  • ከአምላክ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችለው የመጀመሪያው እርምጃ የአምላክን ስም ማወቅና ስሙን መጠቀም ነው። (መዝሙር 9:10፤ ሚልክያስ 3:16) ከአምላክ ጋር እንዲህ ያለ ወዳጅነት መመሥረታችን የሚከተለው ተስፋ እንዲፈጸምልን ያደርጋል፦ “ስለወደደኝ፣ እታደገዋለሁ። ስሜን ስለሚያውቅ እጠብቀዋለሁ።”—መዝሙር 91:14

  • መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ ‘አማልክት’ እና ብዙ ‘ጌቶች’ እንደመኖራቸው መጠን በሰማይም ሆነ በምድር አማልክት ተብለው የሚጠሩ” እንዳሉ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 8:5, 6) ሆኖም ብቸኛውን እውነተኛ አምላክ፣ ይሖዋ በሚለው ስሙ ለይቶ ይጠራዋል።—መዝሙር 83:18

a አንዳንድ የዕብራይስጥ ምሁራን የአምላክ ስም “ያህዌ” ተብሎ መጠራት እንዳለበት ይሰማቸዋል።

b መለኮታዊው ስም በአጭሩ የሚጻፈው “ያህ” ተብሎ ነው፤ ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 50 ጊዜ ያህል ይገኛል። ቃሉ “ሃሌ ሉያ” ወይም “ሃሌሉያህ” በሚለው አገላለጽ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ትርጉሙም “ያህን አወድሱ” ማለት ነው።—ራእይ 19:1 ግርጌ፤ አዲሱ መደበኛ ትርጉም