በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በራእይ ምዕራፍ 17 ላይ የተጠቀሰው ደማቅ ቀይ አውሬ ምን ያመለክታል?

በራእይ ምዕራፍ 17 ላይ የተጠቀሰው ደማቅ ቀይ አውሬ ምን ያመለክታል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በራእይ ምዕራፍ 17 ላይ የተጠቀሰው ደማቅ ቀይ አውሬ የዓለምን መንግሥታት አንድ የማድረግና እነሱን የመወከል ዓላማ ያለውን አንድ ድርጅት ይወክላል። ይህ አውሬ ቀደም ሲል የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው።

የአውሬውን ማንነት ለማወቅ የሚረዱ ነጥቦች

 1.   የፓለቲካ ድርጅት። ይህ ደማቅ ቀይ አውሬ ‘ሰባት ራሶች’ አሉት፤ እነዚህ ራሶች ‘ሰባት ተራሮችን’ እና ‘ሰባት ነገሥታትን’ ወይም መንግሥታትን እንደሚያመለክቱ ተገልጿል። (ራእይ 17:9, 10) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተራሮችና አራዊት መንግሥታትን ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል።—ኤርምያስ 51:24, 25፤ ዳንኤል 2:44, 45፤ 7:17, 23

 2.   ዓለም አቀፉን የፖለቲካ ሥርዓት ይወክላል። ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው አውሬ ዓለም አቀፉን የፖለቲካ ሥርዓት ከሚወክለው በራእይ ምዕራፍ 13 ላይ ከተገለጸው ሰባት ራሶች ያሉት አውሬ ጋር ይመሳሰላል። ሁለቱም አውሬዎች ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ያላቸው ከመሆኑም ሌላ አምላክን የሚሰድቡ ስሞች አሏቸው። (ራእይ 13:1፤ 17:3) ሁለቱ አውሬዎች በጣም የሚመሳሰሉ ከመሆናቸው የተነሳ ይህ የሆነው በአጋጣሚ ነው ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው አውሬ ዓለም አቀፉን የፖለቲካ ሥርዓት የሚወክል ነው።—ራእይ 13:15

 3.   ኃይሉን ያገኘው ከሌሎች መንግሥታት ነው። ይህ ደማቅ ቀይ አውሬ ‘የወጣው’ ወይም የተገኘው ከሌሎች መንግሥታት ነው።—ራእይ 17:11, 17

 4.   ከሃይማኖት ጋር ጥምረት አለው። የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶችን በሙሉ የምታመለክተው ታላቂቱ ባቢሎን በዚህ ደማቅ ቀይ አውሬ ላይ ተቀምጣለች፤ ይህም የሃይማኖት ቡድኖች በአውሬው ላይ ተጽእኖ እንደሚያደርጉበት ያሳያል።—ራእይ 17:3-5

 5.   ለአምላክ ክብር አይሰጥም። አውሬው ‘አምላክን በሚሰድቡ ስሞች’ ተሞልቷል።—ራእይ 17:3

 6.   ለአጭር ጊዜ አይኖርም። ይህ ደማቅ ቀይ አውሬ ለተወሰነ ጊዜ ‘ጥልቁ’ a ውስጥ የሚገባ ማለትም እንቅስቃሴው የሚቋረጥ ቢሆንም መልሶ ከጥልቁ ይወጣል።—ራእይ 17:8

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ

 መጽሐፍ ቅዱስ ደማቅ ቀይ ቀለም ስላለው አውሬ የሚናገረው ትንቢት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይም ሆነ ከእሱ በፊት በነበረው የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ላይ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

 1.   የፖለቲካ ድርጅት። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ‘የሁሉንም አባላቱን እኩልነት’ በማስጠበቅ የፖለቲካውን ሥርዓት ይደግፋል። b

 2.   ዓለም አቀፉን የፖለቲካ ሥርዓት ይወክላል። በ2011 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት ቁጥር 193 ደርሷል። በመሆኑም በዓለም ላይ ካሉት ብሔራትና ሕዝቦች መካከል አብዛኞቹን እንደሚወክል ይናገራል።

 3.   ኃይሉን ያገኘው ከሌሎች መንግሥታት ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የመሠረቱት አባል አገራቱ ከመሆናቸውም ሌላ ያለውን ኃይልና ሥልጣን በሙሉ ያገኘው ከእነሱ ነው።

 4.   ከሃይማኖት ጋር ጥምረት አለው። የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ሃይማኖቶች ድጋፍ ተለይቷቸው አያውቅም። c

 5.   ለአምላክ ክብር አይሰጥም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተቋቋመው ‘በዓለም ዙሪያ ሰላምና ደኅንነት ለማስፈን’ ነው። d ይህን ዓላማ ይዞ መነሳቱ ጥሩ ቢመስልም እንደ እውነቱ ከሆነ አምላክን እየሰደበ ነው፤ ምክንያቱም አምላክ፣ የእሱ መንግሥት ብቻ እንደሚያከናውናቸው የገለጻቸውን ነገሮች እንደሚያደርግ ተናግሯል።—መዝሙር 46:9፤ ዳንኤል 2:44

 6.   ለአጭር ጊዜ አይኖርም። የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የተቋቋመው አንደኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነበር፤ ዓላማው ሰላም ማስፈን የነበረ ቢሆንም በዓለም ዙሪያ ግጭቶችን መከላከል አልቻለም። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1939 ሲፈነዳ አገልግሎት መስጠቱን አቆመ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1945 ሲያበቃ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋቋመ። የዚህ ድርጅት ዓላማ፣ አሠራርና አወቃቀር ከመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል።

a ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ እንደሚገልጸው “ጥልቁ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ወሰን የሌለው ጥልቀትን” ያመለክታል። አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህን ቃል “ጥልቁ ጉድጓድ” በማለት ተርጉሞታል። ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ እስር ቤት ያለን ቦታ ወይም ሁኔታ ለማመልከት ተሠርቶበታል።

b የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ቻርተር አንቀጽ 2 ተመልከት።

c ለምሳሌ ያህል፣ በአሜሪካ የሚገኙ በፕሮቴስታንት ሥር የሚታቀፉ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን የሚወክል ምክር ቤት፣ የቃል ኪዳኑ ማኅበር “የአምላክን መንግሥት በምድር ላይ የሚወክል ፖለቲካዊ ምልክት” እንደሆነ በ1918 ገልጾ ነበር። በ1965 የሂንዱይዝም፣ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ፣ የቡድሂዝም፣ የአይሁድ፣ የእስልምና፣ የካቶሊክና የፕሮቴስታንት እምነት ተወካዮች ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለመጸለይ በሳን ፍራንሲስኮ ተሰብስበው ነበር። በ1979 ደግሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዳግማዊ ጆን ፖል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “ከፍተኛው የሰላምና የፍትሕ መድረክ ሆኖ እንዲቀጥል” ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል።

d የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ቻርተር አንቀጽ 1 ተመልከት።