በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

“የመጨረሻው ዘመን” ምልክት ምንድን ነው?

“የመጨረሻው ዘመን” ምልክት ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” ወይም “የዓለም መጨረሻ” መድረሱን እንድናውቅ የሚያስችሉንን ክንውኖችና ሁኔታዎች ይገልጻል። (ማቴዎስ 24:3 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጊዜ ‘የመጨረሻውን ዘመን፣’ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ እንዲሁም ‘የፍጻሜው ዘመን’ በማለት ይጠራዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1 አዲሱ መደበኛ ትርጉም፤ ዳንኤል 8:19) የመጨረሻዎቹን ቀናት ወይም የመጨረሻው ዘመን አስመልክቶ በተነገሩት ትንቢቶች ላይ የተጠቀሱ ዋና ዋና ክንውኖች ከዚህ ቀጥሎ ተዘርዝረዋል፦

 • መጠነ ሰፊ ጦርነት።—ማቴዎስ 24:7፤ ራእይ 6:4

 • ረሃብ።—ማቴዎስ 24:7፤ ራእይ 6:5, 6

 • ታላላቅ የመሬት መንቀጥቀጦች።—ሉቃስ 21:11

 • ቸነፈር ወይም አስከፊ ወረርሽኝ።—ሉቃስ 21:11

 • የወንጀል መስፋፋት።—ማቴዎስ 24:12

 • ሰዎች ምድርን ማበላሸታቸው።—ራእይ 11:18

 • የሰዎች ባሕርይ መበላሸት፤ ይኸውም ሰዎች “የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ . . . ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ” ይሆናሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-4

 • ሰዎች “ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው” እንዲሁም ልጆች “ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ” በመሆናቸው ምክንያት ቤተሰብ መፈራረሱ።—2 ጢሞቴዎስ 3:2, 3

 • ብዙ ሰዎች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር መቀዝቀዙ።—ማቴዎስ 24:12

 • በግልጽ የሚታይ ሃይማኖታዊ ግብዝነት።—2 ጢሞቴዎስ 3:5

 • ከመጨረሻዎቹ ቀናት ጋር የተያያዙ ትንቢቶችን ጨምሮ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ያለው ግንዛቤ መጨመር።—ዳንኤል 12:4

 • የመንግሥቱ ምሥራች በዓለም ዙሪያ መሰበክ።—ማቴዎስ 24:14

 • ብዙዎች መጨረሻው እየቀረበ መሆኑን ለሚያሳዩት ማስረጃዎች ግድየለሽ እንዲሁም ፌዘኛ መሆናቸው።—ማቴዎስ 24:37-39፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 4.

 • ከእነዚህ ትንቢቶች መካከል የተወሰኑት ወይም አብዛኞቹ ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም በአንድ ወቅት ላይ መፈጸማቸው።—ማቴዎስ 24:33

የምንኖረው “በመጨረሻው ዘመን” ውስጥ ነው?

አዎ። በዓለም ላይ የተፈጸሙ ክንውኖች እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር የመጨረሻው ዘመን በ1914 እንደጀመረ ይጠቁማሉ። በዚህ ጊዜ የአምላክ መንግሥት በሰማይ መግዛት ጀምሯል፤ ይህ መንግሥት መጀመሪያ ላይ ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ ሰይጣን ዲያብሎስንና አጋንንቱን ከሰማይ አባሮ እንቅስቃሴያቸው ምድር ላይ ብቻ የተገደበ እንዲሆን ማድረግ ነው። (ራእይ 12:7-12) የመጨረሻዎቹን ቀናት “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” እንዲሆኑ ያደረጉት የሰዎች መጥፎ ባሕርያትና ድርጊቶች ሰይጣን በሰው ልጆች ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ያሳያሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:1