በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

‘የመንግሥተ ሰማያት ቁልፎች’ ምንድን ናቸው?

‘የመንግሥተ ሰማያት ቁልፎች’ ምንድን ናቸው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ‘የመንግሥተ ሰማያት ቁልፎች’ ሰዎች “ወደ አምላክ መንግሥት [መግባት]” እንዲችሉ መንገድ የመክፈት ሥልጣንን ያመለክታሉ። (ማቴዎስ 16:19፤ የሐዋርያት ሥራ 14:22) a ኢየሱስ ለጴጥሮስ “የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች” ሰጥቶታል። ይህም ማለት ጴጥሮስ ታማኝ የሆኑ ሰዎች የአምላክን ቅዱስ መንፈስ በመቀበል ወደ መንግሥተ ሰማያት የመግባት መብት የሚያገኙት እንዴት እንደሆነ የሚገልጸውን መረጃ ለሌሎች የመግለጥ ሥልጣን ተሰጥቶታል ማለት ነው።

እነዚህ ቁልፎች ጥቅም ላይ የዋሉት እንዴት ነው?

 ጴጥሮስ አምላክ የሰጠውን ሥልጣን በመጠቀም ሦስት ቡድኖች ወደ አምላክ መንግሥት እንዲገቡ መንገድ ከፍቷል፦

  1.   አይሁዳውያንና ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች። ኢየሱስ ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጴጥሮስ፣ በአንድ ቦታ ተሰብስበው ለነበሩ የአይሁድ እምነት ተከታዮች አምላክ በመንግሥቱ እንዲገዛ ኢየሱስን የመረጠ መሆኑን አምነው እንዲቀበሉ አበረታቷቸው ነበር። ጴጥሮስ መዳን ከፈለጉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ነግሯቸዋል። በዚህ መልኩ ወደ አምላክ መንግሥት መግባት የሚችሉበትን መንገድ ከፈተላቸው፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ‘ቃሉን ተቀበሉ።’—የሐዋርያት ሥራ 2:38-41

  2.   ሳምራውያን። በኋላም ጴጥሮስ ወደ ሳምራውያን ተላከ። b ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር በመሆን ‘መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ በጸለዩላቸው’ ወቅት አንዱን የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ ተጠቅሟል። (የሐዋርያት ሥራ 8:14-17) ይህም፣ ሳምራውያን ወደ አምላክ መንግሥት መግባት እንዲችሉ መንገድ ከፍቷል።

  3.   አሕዛብ። ኢየሱስ ከሞተ ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ አምላክ፣ አሕዛብም (አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች) ወደ አምላክ መንግሥት የመግባት አጋጣሚ እንደሚያገኙ ለጴጥሮስ ገለጠለት። በምላሹም ጴጥሮስ ለአሕዛብ የሰበከ ሲሆን መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ክርስቲያን የሚሆኑበትንና ወደ አምላክ መንግሥት መግባት የሚችሉበትን መንገድ በመክፈት አንዱን ቁልፍ ተጠቅሞበታል።—የሐዋርያት ሥራ 10:30-35, 44, 45

“ወደ አምላክ መንግሥት መግባት” ሲባል ምን ማለት ነው?

 ቃል በቃል ‘ወደ አምላክ መንግሥት የሚገቡ’ ሰዎች ወደ ሰማይ በመሄድ ከኢየሱስ ጋር አብረው ይገዛሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በዙፋን እንደሚቀመጡ’ እንዲሁም ‘በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው እንደሚገዙ’ ይናገራል።—ሉቃስ 22:29, 30፤ ራእይ 5:9, 10

የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች በተመለከተ ብዙዎች ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ወደ ሰማይ ማን እንደሚገባ የሚወስነው ጴጥሮስ ነው።

 እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ ‘በሕያዋንና በሙታን ላይ የሚፈርደው’ ጴጥሮስ ሳይሆን ክርስቶስ ኢየሱስ እንደሆነ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 4:1, 8፤ ዮሐንስ 5:22) እንዲያውም ጴጥሮስ ራሱ አምላክ ‘በሕያዋንና በሙታን ላይ ፈራጅ አድርጎ የሾመው’ ኢየሱስን እንደሆነ ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 42

 የተሳሳተ አመለካከት፦ የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች መቼ መጠቀም እንደሚገባ የመወሰን ሥልጣን ያለው ጴጥሮስ ነው፤ በመሆኑም በሰማይ ላይ የሚደረገው ውሳኔ በጴጥሮስ ውሳኔ ላይ የተመካ ነው።

 እውነታው፦ ኢየሱስ ስለ መንግሥተ ሰማያት በተናገረበት ወቅት ለጴጥሮስ እንዲህ ብሎት ነበር፦ “በምድር ያሰርኸው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የፈታኸው ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።” (ማቴዎስ 16:19 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) አንዳንድ ሰዎች ይህ ሐሳብ በሰማይ ላይ የሚደረጉ ውሳኔዎች በጴጥሮስ ውሳኔዎች ላይ የተመኩ መሆናቸውን እንደሚያመለክት ይሰማቸዋል፤ ሆኖም እዚህ ላይ የተሠራባቸው የግሪክኛ ግሶች የሚያሳዩት የጴጥሮስ ውሳኔዎች በሰማይ የተደረጉትን እንደሚከተሉ እንጂ እንደሚቀድሙ አይደለም።

 መጽሐፍ ቅዱስ ሌላ ቦታ ላይ ጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች ሲጠቀም ከሰማይ የተሰጠውን አመራር እንደተከተለ ይናገራል። ለምሳሌ ሦስተኛውን ቁልፍ የተጠቀመው አምላክ የሰጠውን መመሪያ ተከትሎ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 10:19, 20

a “ቁልፍ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሥልጣንንና ኃላፊነትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።—ኢሳይያስ 22:20-22፤ ራእይ 3:7, 8

b ሳምራውያን የሚከተሉት ሃይማኖት ከአይሁድ እምነት የተለየ ቢሆንም በሙሴ ሕግ ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ ትምህርቶችና ሥርዓቶች ይቀበሉ ነበር።