በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

“ዓይን ስለ ዓይን” ሲባል ምን ማለት ነው?

“ዓይን ስለ ዓይን” ሲባል ምን ማለት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ትእዛዝ አምላክ በሙሴ በኩል ለጥንት እስራኤላውያን ከሰጣቸው ሕግ አንዱ ነው፤ ኢየሱስም በተራራው ስብከቱ ላይ ጠቅሶታል። (ማቴዎስ 5:38፤ ዘፀአት 21:24, 25፤ ዘዳግም 19:21) ይህ ሕግ ለጥፋተኞች የሚሰጠው ፍርድ ከጥፋታቸው ጋር የሚመጣጠን መሆን እንዳለበት ያሳያል። a

 ይህ ሕግ ተፈጻሚ የሚሆነው አንድ ሰው በሌላው ላይ ሆን ብሎ ጉዳት ሲያደርስ ነው። እንደዚህ ዓይነት ድርጊት የሚፈጽምን ሰው በተመለከተ የሙሴ ሕግ እንዲህ ይላል፦ “ስብራት ስለ ስብራት፣ ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ ይሁን፤ በሰውየው ላይ ያደረሰው ዓይነት ጉዳት በእሱ ላይ እንዲደርስ ይደረግ።”—ዘሌዋውያን 24:20

 “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ ዓላማው ምን ነበር?

 “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ ሰዎች ሲበደሉ የበቀል እርምጃ እንዲወስዱ የሚፈቅድ አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ፣ የተሾሙ ዳኞች በጣም ጥብቅ ወይም ልል ሳይሆኑ ተገቢ የሆነ የቅጣት ፍርድ እንዲያስተላልፉ የሚረዳ ነው።

 ከዚህም ሌላ ሕጉ በሌሎች ላይ ሆን ብለው ጉዳት ለሚያደርሱ ወይም ይህን ለማድረግ ለሚያሴሩ ሰዎች እንደ ማስጠንቀቂያ ያገለግል ነበር። ሕጉ እንዲህ ይላል፦ “ሌሎችም ይህን [አምላክ የወሰደውን ፍትሐዊ እርምጃ] ሲሰሙ ይፈራሉ፤ በመካከልህም እንዲህ ያለ መጥፎ ነገር ፈጽሞ ዳግመኛ አያደርጉም።”—ዘዳግም 19:20

 “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ በክርስቲያኖች ላይ ይሠራል?

 አይሠራም፤ ክርስቲያኖች በዚህ ሕግ እንዲመሩ አይጠበቅባቸውም። “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ደንብ የሙሴ ሕግ ክፍል ሲሆን የሙሴ ሕግ ደግሞ ኢየሱስ መሥዋዕት ሆኖ ሲሞት ተወግዷል።—ሮም 10:4

 ያም ቢሆን ሕጉ ስለ አምላክ አስተሳሰብ ለማወቅ ያስችለናል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ለፍትሕ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ እንማራለን። (መዝሙር 89:14) እንዲሁም ከፍትሕ ጋር በተያያዘ የአምላክ መሥፈርት ምን እንደሆነ ይኸውም ጥፋት የሠሩ ሰዎች “በተገቢው መጠን” መቀጣት እንዳለባቸው ይጠቁማል።—ኤርምያስ 30:11

 “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለውን ሕግ በተመለከተ የተሳሳቱ አመለካከቶች

 የተሳሳተ አመለካከት፦ “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ ጭካኔ የሚንጸባረቅበት ነው።

 እውነታው፦ ሕጉ ፍትሕ እንዲፈጸም ሲባል ጭካኔ የሚንጸባረቅበት ቅጣት እንዲበየን አይፈቅድም። ከዚህ ይልቅ በሕጉ መሠረት፣ ቅጣት ከመበየኑ በፊት ብቃት ያላቸው ዳኞች ጉዳዩን መመርመር እንዲሁም ጥፋቱ ሆን ተብሎ የተሠራ መሆን አለመሆኑን ማጣራት ይኖርባቸዋል፤ ሕጉ በትክክል ተግባራዊ ሆኗል ሊባል የሚችለው እንዲህ ካደረጉ ብቻ ነው። (ዘፀአት 21:28-30፤ ዘኁልቁ 35:22-25) “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ ከተፈጸመው ጥፋት ጋር የማይመጣጠን ቅጣት እንዳይተላለፍ ይረዳል።

 የተሳሳተ አመለካከት፦ “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ ማብቂያ የሌለው በቀልን ያበረታታል።

 እውነታው፦ የሙሴ ሕግ “የሕዝብህን ልጆች አትበቀል፤ በእነሱም ላይ ቂም አትያዝ” ይላል። (ዘሌዋውያን 19:18) ሕጉ ሰዎች የራሳቸውን የበቀል እርምጃ እንዲወስዱ ከማበረታታት ይልቅ በአምላክና ፍትሕን ለማስፈን ሲል ባቋቋመው የሕግ ሥርዓት ላይ እንዲተማመኑ ያበረታታ ነበር።—ዘዳግም 32:35

a ይህ መሠረታዊ ሐሳብ፣ አንዳንድ ጊዜ በላቲን ሌክስ ታሊዮኒስ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በአንዳንድ የጥንት ማኅበረሰቦች የሕግ ሥርዓት ውስጥም ይገኛል።