በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ስለ ኢየሱስ የሚተርኩት ዘገባዎች የተጻፉት መቼ ነው?

ስለ ኢየሱስ የሚተርኩት ዘገባዎች የተጻፉት መቼ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ስለ ኢየሱስ ሕይወት የጻፈውን ዘገባ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ያየው ሰውም ምሥክርነት ሰጥቷል፤ ምሥክርነቱም እውነት ነው፤ እናንተም ታምኑ ዘንድ ይህ ሰው እውነተኛ ነገር እንደሚናገር ያውቃል።”—ዮሐንስ 19:35

 ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ እና ዮሐንስ የጻፏቸው የወንጌል ዘገባዎች ትክክለኛ ናቸው የምንልበት አንዱ ምክንያት እነዚህ ጸሐፊዎች፣ ወንጌሎቹን በጻፉበት ወቅት ታሪኮቹን የሚያውቁ የዓይን ምሥክሮች በሕይወት መኖራቸው ነው። አንዳንድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት የማቴዎስ ወንጌል የተጻፈው ክርስቶስ ከሞተ ከስምንት ዓመት በኋላ ማለትም በ41 ዓ.ም. ገደማ ነበር። በርካታ ምሁራን የማቴዎስ ወንጌል ከዚህ ጊዜ በኋላ እንደተጻፈ ይናገራሉ፤ ያም ሆነ ይህ ሁሉም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ውስጥ እንደተጻፉ ብዙዎች ይስማማሉ።

 ኢየሱስ በሕይወት እያለ የሚያውቁት እንዲሁም ሞቱንና ትንሣኤውን የተመለከቱ ሰዎች እነዚህ መጻሕፍት በተጻፉበት ወቅት በሕይወት ነበሩ፤ በመሆኑም የወንጌል ዘገባዎቹ ትክክል መሆናቸውን ማረጋገጥ ይችላሉ። እንዲሁም በወንጌሎቹ ላይ ትክክል ያልሆነ ሐሳብ ቢሰፍር ኖሮ ይህን ማጋለጥ ይችሉ ነበር። ፕሮፌሰር ፍሬድሪክ ብሩስ እንዲህ ብለዋል፦ “የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ስብከት ትክክለኛ ለመሆኑ ማስረጃ ከሚሆኑት ጠንካራ ነጥቦች አንዱ የሚሰብኩትን ነገር አድማጮቻቸው እንደሚያውቁት በልበ ሙሉነት መናገር መቻላቸው ነበር፤ ሐዋርያት ‘ለዚህ ነገር እኛ ምሥክሮች ነን’ ከማለት አልፈው ‘እናንተ ራሳችሁ እንደምታውቁት’ በማለት ይናገሩ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 2:22)።”