በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወርቃማው ሕግ ምንድን ነው?

ወርቃማው ሕግ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 “ወርቃማው ሕግ” የሚለው አገላለጽ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ብዙ ሰዎች ይህን አገላለጽ የሚጠቀሙት ኢየሱስ ያስተማረውን አንድ የሥነ ምግባር ደንብ ለማመልከት ነው። ኢየሱስ ታዋቂ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ የሚከተለውን የሥነ ምግባር ደንብ ሰጥቶ ነበር፦ “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው።”—ማቴዎስ 7:12፤ ሉቃስ 6:31

 ወርቃማው ሕግ ትርጉሙ ምንድን ነው?

 ወርቃማው ሕግ፣ ሌሎች እንዲይዙን በምንፈልግበት መንገድ እነሱን እንድንይዝ ያበረታታናል። ለምሳሌ አብዛኞቻችን ሌሎች ሰዎች አክብሮት፣ ደግነትና ፍቅር ሲያሳዩን ደስ ይለናል። በመሆኑም እኛም ለሌሎች “እንዲሁ” ልናደርግላቸው ይገባል።—ሉቃስ 6:31

 ወርቃማው ሕግ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

 ወርቃማው ሕግ ከሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ጋር በተያያዘ ይሠራል። ለምሳሌ፦

 ወርቃማው ሕግ በተለምዶ ብሉይ ኪዳን በሚባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ የሚገኘውን አብዛኛውን ሐሳብ ጠቅልሎ የያዘ ነው። ኢየሱስ ስለ ወርቃማው ሕግ ሲናገር “ሕጉም [የመጀመሪያዎቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት] ሆነ የነቢያት ቃል [የትንቢት መጻሕፍት] የሚሉት ይህንኑ ነው” ብሏል። (ማቴዎስ 7:12) በሌላ አባባል ወርቃማው ሕግ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ በዋነኝነት የተገለጸውን መሠረታዊ ሐሳብ ጠቅለል አድርጎ ይዟል፤ ይህ ሐሳብ ‘ባልንጀራህን ውደድ’ የሚለው ነው።—ሮም 13:8-10

 ወርቃማው ሕግ፣ ሰጥቶ የመቀበል ጉዳይ ነው?

 አይደለም። ወርቃማው ሕግ ትኩረት የሚያደርገው በመስጠት ላይ ነው። ኢየሱስ ወርቃማውን ሕግ ባስተማረበት ወቅት እየተናገረ የነበረው በጥቅሉ ሰዎችን እንዴት መያዝ እንዳለብን ብቻ አይደለም፤ ከዚህም ባለፈ ጠላቶቻችንን እንኳ እንዴት ልንይዝ እንደሚገባ እየገለጸ ነበር። (ሉቃስ 6:27-31, 35) ከዚህ አንጻር ወርቃማው ሕግ ለሁሉም ሰው መልካም እንድናደርግ የሚያበረታታ ነው።

 ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

  1.  1. አስተዋይ ሁኑ። ለሌሎች ሰዎች ትኩረት ስጡ። ለምሳሌ፣ አንድ ሰው ከባድ ሸክም እንደያዘ ትመለከቱ፣ ጎረቤታችሁ ታምሞ ሆስፒታል እንደገባ ትሰሙ ወይም የሥራ ባልደረባችሁ እንደከፋው ታስተውሉ ይሆናል። ‘ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ትኩረት የምትሰጡ’ ከሆነ ሌሎችን የሚጠቅም ነገር መናገር ወይም ማድረግ የምትችሉበት አጋጣሚ ማግኘታችሁ አይቀርም።—ፊልጵስዩስ 2:4

  2.  2. የሌላውን ስሜት ለመጋራት ጥረት አድርጉ። ራሳችሁን በሌሎች ቦታ ለማስቀመጥ ሞክሩ። እናንተ በዚያ ሁኔታ ውስጥ ብትሆኑ ኖሮ ምን ይሰማችሁ ነበር? (ሮም 12:15) የሌሎችን ስሜት ለመረዳት ጥረት ስታደርጉ እነሱን ለመርዳት መነሳሳታችሁ አይቀርም።

  3.  3. እንደ ሁኔታው ማስተካከያ አድርጉ። እያንዳንዱ ሰው የተለያየ እንደሆነ አትርሱ። ሌሎች እንዲደረግላቸው የሚፈልጉት ነገር እናንተ እንዲደረግላችሁ ከምትፈልጉት የተለየ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ልታደርጉላቸው የምትችሏቸው የተለያዩ ነገሮች ቢኖሩም ይበልጥ የሚያስፈልጋቸውን ነገር መርጣችሁ አድርጉላቸው።—1 ቆሮንቶስ 10:24