በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ክርስቲያን ነን የሚሉ ሃይማኖታዊ ቡድኖች የበዙት ለምንድን ነው?

ክርስቲያን ነን የሚሉ ሃይማኖታዊ ቡድኖች የበዙት ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ሰዎች የተለያዩ “የክርስትና” ሃይማኖታዊ ቡድኖችን ያቋቋሙት ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማራቸውን ትምህርቶች ተጠቅመው ነው። ይሁን እንጂ፣ እውነተኛው የክርስትና ሃይማኖት አንድ ብቻ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል። እስቲ እዚህ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ የሚያደርጉንን ሦስት ምክንያቶች ብቻ እንመልከት።

  1.   ኢየሱስ እሱ ያስተማረውን ትምህርት “እውነት” በማለት የጠራው ሲሆን የጥንት ክርስቲያኖች ሃይማኖታቸውን “እውነት” ይሉት ነበር። (ዮሐንስ 8:32፤ 2 ጴጥሮስ 2:2፤ 2 ዮሐንስ 4፤ 3 ዮሐንስ 3) ይህ መጠሪያ እንደሚያሳየው ከኢየሱስ ትምህርቶች ጋር የሚቃረን ሐሳብ የሚያስተምሩ የሃይማኖት ድርጅቶች እውነተኛ ክርስቲያኖች አይደሉም።

  2.   መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ክርስቲያኖች ‘ንግግራቸው አንድ እንዲሆን’ ያስተምራል። (1 ቆሮንቶስ 1:10) ይሁንና ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙዎቹ ቡድኖች ‘ክርስቲያን መሆን ሲባል ምን ማለት ነው’ ከሚለው አንስቶ መሠረታዊ ለሆኑት ትምህርቶች የሚሰጡት ማብራሪያ እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው። እንዲህ ያሉ ሃይማኖታዊ ቡድኖች በጠቅላላ ትክክለኛ ሊሆኑ አይችሉም።—1 ጴጥሮስ 2:21

  3.   ኢየሱስ ብዙ ሰዎች ክርስቲያኖች እንደሆኑ እንደሚናገሩ ሆኖም እሱ የሰጠውን ትእዛዛት እንደማይከተሉ ትንቢት ተናግሯል፣ በተጨማሪም እንዲህ ያሉ ሰዎችን እንደማይቀበላቸው ገልጿል። (ማቴዎስ 7:21-23፤ ሉቃስ 6:46) የራሳቸውን ጥቅም ለማራመድ ሲሉ እውነተኛውን አምልኮ በሚበክሉ የሃይማኖት መሪዎች የተታለሉ ሰዎች አሉ። (ማቴዎስ 7:15) ሌሎች ሰዎች ግን ሆን ብለው የውሸት ክርስትናን መከተል ይመርጣሉ፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች መስማት የሚፈልጉት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን እውነት ሳይሆን እነሱ መስማት የሚፈልጉትን የሚነግራቸውን ሰው ነው።—2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4

 ኢየሱስ ስለ ስንዴውና እንክርዳዱ በተናገረው ምሳሌ ላይ በእውነተኛው ክርስትና ላይ ዓመፅ (ክህደት) እንደሚነሳ ትንቢት ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:24-30, 36-43) በትንቢቱ መሠረት ለረጅም ዘመን እውነተኛ ክርስቲያኖችን ከሐሰተኛ ክርስቲያኖች መለየት ፈጽሞ የማይቻል ይሆናል። ልክ ኢየሱስ እንደተናገረው ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ክህደቱ ተስፋፋ። (የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30) የክህደት ትምህርቶች ዓይነታቸው የተለያየ ቢሆንም አስመሳይ የሆኑት የክርስትና ቡድኖች በሙሉ “ከእውነት ርቀዋል።”—2 ጢሞቴዎስ 2:18

 በተጨማሪም ኢየሱስ በእውነተኛውና በሐሰተኛው ክርስትና መካከል ያለው ልዩነት ውሎ አድሮ ግልጽ እንደሚሆን ትንቢት ተናግሯል። ይህ የሆነው በእኛ ዘመን ማለትም ‘በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ነው።—ማቴዎስ 13:30, 39