በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ መኳኳልንና ጌጣጌጥ ማድረግን በተመለከተ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ መኳኳልንና ጌጣጌጥ ማድረግን በተመለከተ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ በዝርዝር ባይናገርም መኳኳልን እንዲሁም ጌጣጌጦችንም ሆነ ሌላ ዓይነት መዋቢያ ማድረግን አያወግዝም። ይሁን እንጂ በውጫዊ ውበት ላይ ከማተኮር ይልቅ “የማይጠፋውን ጌጥ ይኸውም በአምላክ ፊት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን የሰከነና ገር መንፈስ [የተላበሱ]” መሆንን ያበረታታል።—1 ጴጥሮስ 3:3, 4

መጽሐፍ ቅዱስ ራስን ማስዋብን አያወግዝም

  •   በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ ታማኝ ሴቶች ራሳቸውን ያስውቡ ነበር። የአብርሃም ልጅ የሆነውን ይስሐቅን ያገባችው ርብቃ፣ አማቿ ከሚሆነው ከአብርሃም በስጦታ መልክ የተበረከተላትን የወርቅ የአፍንጫ ቀለበት፣ የወርቅ አምባሮች እንዲሁም ሌሎች ውድ ጌጣጌጦች አድርጋ ነበር። (ዘፍጥረት 24: 22, 30, 53) በተመሳሳይም አስቴር የፋርስ ግዛት ንግሥት ሆና ለመመረጥ ብቁ እንድትሆን ሲባል የተደረገላትን “የውበት እንክብካቤ” ተቀብላለች። (አስቴር 2:7, 9, 12) ይህ እንክብካቤ ደግሞ “መዋቢያዎችን” እንዲሁም “የተለያዩ ዓይነት መኳኳያዎችን” መጠቀምን የሚያካትት ሳይሆን አይቀርም።—ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን፤ ኢዚ ቱ ሪድ ቨርሽን

  •   መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ የሆኑ ነገሮችን ለመግለጽ ጌጣጌጦችን እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቀማል። ለምሳሌ ጥሩ ምክር የሚሰጥ ሰው “የሚሰማ ጆሮ ላለው እንደ ወርቅ ጉትቻ” እንደሆነ ተገልጿል። (ምሳሌ 25:12) በተጨማሪም አምላክ የእስራኤልን ብሔር የያዘበትን መንገድ ለመግለጽ የእጅ አምባር፣ የአንገት ሐብልና የጆሮ ጉትቻ በመስጠት ሙሽራውን ከሚያስውብ ባል ጋር ራሱን አነጻጽሯል። እነዚህ ጌጣጌጦች ብሔሩን “እጅግ ውብ” አድርገውት ነበር።—ሕዝቅኤል 16:11-13

ብዙዎች መኳኳልንና ጌጣጌጥ ማድረግን በተመለከተ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

 የተሳሳተ አመለካከት፦ መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ጴጥሮስ 3:3 ላይ ‘ሹሩባ መሠራትንና የወርቅ ጌጣጌጦች ማድረግን’ ያወግዛል።

 እውነታው፦ በዙሪያው ካለው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ እዚህ ላይ እያጎላ ያለው ውስጣዊ ውበት፣ ካማረ ውጫዊ ገጽታ ወይም ጌጣጌጦችን ከማድረግ የላቀ ዋጋ እንዳለው ነው። (1 ጴጥሮስ 3:3-6) ይህን የመሰለው ንጽጽር በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም ውስጥ ይገኛል።—1 ሳሙኤል 16:7፤ ምሳሌ 11:22፤ 31:30፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ክፉ የሆነችው ንግሥት ኤልዛቤል “ዓይኖቿን ተኩላ” የነበረ መሆኑ እንዲህ ያሉ መዋቢያዎችን መጠቀም ስህተት እንደሆነ ያሳያል።—2 ነገሥት 9:30

 እውነታው፦ ኤልዛቤል የተፈረደባት መተተኛና ነፍሰ ገዳይ በመሆኗ እንጂ በውጫዊ ገጽታዋ ምክንያት አልነበረም።—2 ነገሥት 9:7, 22, 36, 37