በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እውነተኛውን ሃይማኖት ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

እውነተኛውን ሃይማኖት ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛውን ሃይማኖት በሚከተሉትና በማይከተሉት ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት በምሳሌያዊ መንገድ ሲያስረዳ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ሰዎች ከእሾህ ወይን፣ ከአሜኬላስ በለስ ይለቅማሉ?” ይላል። (ማቴዎስ 7:16) አንድ የወይን ዛፍ ከእሾህ ቁጥቋጦ በፍሬው እንደሚለይ ሁሉ እውነተኛው ሃይማኖትም ከሐሰተኛው የሚለየው በሚያፈራቸው ፍሬዎች ወይም ቀጥሎ በተዘረዘሩት ነጥቦች ነው።

  1.   እውነተኛው ሃይማኖት የሚያስተምረው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት እንጂ የሰዎችን ፍልስፍና አይደለም። (ዮሐንስ 4:24፤ 17:17) ይህም ስለ ነፍስና በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ስለማግኘት የሚናገረውን ሃይማኖታዊ እውነት ይጨምራል። (መዝሙር 37:29፤ ኢሳይያስ 35:5, 6፤ ሕዝቅኤል 18:4) የሐሰት ሃይማኖቶች የሚያስተምሩትን ውሸት ከማጋለጥም ወደኋላ አይልም።—ማቴዎስ 15:9፤ 23:27, 28

  2.   እውነተኛው ሃይማኖት፣ ሰዎች ስለ አምላክ እንዲያውቁ ይረዳል፤ ይህ ደግሞ ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም ማሳወቅን ይጨምራል። (መዝሙር 83:18፤ ኢሳይያስ 42:8፤ ዮሐንስ 17:3, 6) አምላክ ሚስጥራዊ እንደሆነ ወይም ሊቀረብ እንደማይችል አያስተምርም፤ ከዚህ ይልቅ ከእሱ ጋር ዝምድና እንድንመሠርት እንደሚፈልግ ያስተምራል።—ያዕቆብ 4:8

  3.   እውነተኛው ሃይማኖት፣ አምላክ መዳን እንድናገኝ ዝግጅት ያደረገው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንደሆነ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። (የሐዋርያት ሥራ 4:10, 12) የእውነተኛው ሃይማኖት ተከታዮችም ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ ለመፈጸምና የእሱን ምሳሌ ለመከተል ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።—ዮሐንስ 13:15፤ 15:14

  4.   እውነተኛው ሃይማኖት፣ የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ እንደሆነ አድርጎ የሚመለከተው የአምላክን መንግሥት ነው። የእውነተኛው ሃይማኖት ተከታዮችም ስለዚህ መንግሥት ለሰዎች ይናገራሉ።—ማቴዎስ 10:7፤ 24:14

  5.   እውነተኛው ሃይማኖት፣ ሰዎች ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዲያሳዩ ያስተምራል። (ዮሐንስ 13:35) ሰዎች ዘራቸው፣ ባሕላቸው፣ ቋንቋቸው ወይም ያደጉበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን መከበር እንዳለባቸውና ልንቀበላቸው እንደሚገባ ያስተምራል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) የእውነተኛው ሃይማኖት ተከታዮች ለሰዎች ፍቅር ስላላቸው በጦርነት ላይ አይሳተፉም።—ሚክያስ 4:3፤ 1 ዮሐንስ 3:11, 12

  6.   እውነተኛው ሃይማኖት፣ ገንዘብ የሚከፈላቸው ቀሳውስት የሉትም፤ የትኛውም አገልጋይ ሃይማኖታዊ የማዕረግ ስም አይሰጠውም።—ማቴዎስ 23:8-12፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3

  7.   እውነተኛው ሃይማኖት፣ ከፖለቲካ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ ነው። (ዮሐንስ 17:16፤ 18:36) የእውነተኛው ሃይማኖት ተከታዮች የሚኖሩበትን አገር መንግሥት ያከብራሉ እንዲሁም ይታዘዛሉ። ይህም “የቄሳር [የመንግሥት ባለ ሥልጣናትን ያመለክታል] የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ጋር ይስማማል።—ማርቆስ 12:17፤ ሮም 13:1, 2

  8.   እውነተኛ ሃይማኖት፣ እንዲሁ አንድን የአምልኮ ሥርዓት በዘልማድ የመፈጸም ጉዳይ አይደለም። የእውነተኛው ሃይማኖት ተከታዮች የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መመሪያዎች በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፍ ተግባራዊ ያደርጋሉ። (ኤፌሶን 5:3-5፤ 1 ዮሐንስ 3:18) አምላክን የሚያመልኩት ግዴታ ስለሆነባቸው አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ‘ደስተኛውን አምላክ’ በማምለክ ደስታ ያገኛሉ።—1 ጢሞቴዎስ 1:11

  9.   እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች ቁጥራቸው ትንሽ ነው። (ማቴዎስ 7:13, 14) የእውነተኛው ሃይማኖት ተከታዮች የአምላክን ፈቃድ በማድረጋቸው ሌሎች ሰዎች ይንቋቸዋል፣ ያሾፉባቸዋል አልፎ ተርፎም ስደት ያደርሱባቸዋል።—ማቴዎስ 5:10-12

የአንድ ሃይማኖት እውነተኛነት በእኛ ምርጫ ላይ የተመካ አይደለም

 አንድን ሃይማኖት እኛ ስለወደድነው ብቻ ትክክል ነው ብሎ መደምደም አደገኛ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች “ከራሳቸው ፍላጎት ጋር በሚስማማ ሁኔታ ጆሯቸውን እንዲኮረኩሩላቸው በዙሪያቸው [ሃይማኖታዊ] አስተማሪዎችን” የሚሰበስቡበት ጊዜ እንደሚመጣ ትንቢት ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 4:3) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በመራቅ “በአምላካችንና በአባታችን ዓይን ንጹሕና ያልረከሰ ሃይማኖት” መከተል እንዳለብን ይመክረናል።—ያዕቆብ 1:27 የግርጌ ማስታወሻ፤ ዮሐንስ 15:18, 19