በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እንስሳት ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?

እንስሳት ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ምድር ላይ ብዙ ፍጥረታት ቢኖሩም ወደ ሰማይ የሚሄዱት ጥቂት ሰዎች ብቻ እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። (ራእይ 14:1, 3) እነዚህ ሰዎች ወደ ሰማይ የሚሄዱት ነገሥታትና ካህናት ሆነው ከኢየሱስ ጋር ለመግዛት ነው። (ሉቃስ 22:28-30፤ ራእይ 5:9, 10) አብዛኞቹ ሰዎች ግን ከሞት ተነስተው ምድር ላይ በገነት ይኖራሉ።—መዝሙር 37:11, 29

 መጽሐፍ ቅዱስ ውሾችን ጨምሮ የቤት እንስሳት ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ አንድም ቦታ ላይ አይናገርም፤ ደግሞም ይህ የሆነበት በቂ ምክንያት አለ። እንስሳት “የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች” ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ሊያሟሉ አይችሉም። (ዕብራውያን 3:1) ከእነዚህ ብቃቶች መካከል እውቀት፣ እምነትና የአምላክን ትእዛዛት መጠበቅ ይገኙበታል። (ማቴዎስ 19:17፤ ዮሐንስ 3:16፤ 17:3) ለዘላለም የመኖር ተስፋ ኖሯቸው የተፈጠሩት ሰዎች ብቻ ናቸው።—ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:22, 23

 ምድር ላይ ያሉ ፍጥረታት ወደ ሰማይ ለመሄድ ትንሣኤ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:42) መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በፊት የተለያዩ ትንሣኤዎች እንደተከናወኑ ይገልጻል። (1 ነገሥት 17:17-24፤ 2 ነገሥት 4:32-37፤ 13:20, 21፤ ሉቃስ 7:11-15፤ 8:41, 42, 49-56፤ ዮሐንስ 11:38-44፤ የሐዋርያት ሥራ 9:36-42፤ 20:7-12) ያም ቢሆን ከሞት የተነሱት በሙሉ ሰዎች ናቸው፤ አንድም እንስሳ ከሞት እንደተነሳ የሚገልጽ ዘገባ አናገኝም።

 እንስሳት ነፍስ አላቸው?

 የላቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ሰዎችም ሆኑ እንስሳት ነፍስ እንደሆኑ ነው። (ዘኁልቁ 31:28) የመጀመሪያው ሰው አዳም ሲፈጠር ነፍስ አልተሰጠውም፤ ከዚህ ይልቅ እሱ ራሱ “ሕያው ነፍስ ሆነ።” (ዘፍጥረት 2:7 የግርጌ ማስታወሻ) ነፍስ ሲባል ሁለት ነገሮችን ይኸውም ‘የምድር አፈርን’ እና ‘የሕይወት እስትንፋስን’ የያዘ ነው።

 ነፍስ ትሞታለች?

 አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ እንደምትሞት ይናገራል። (ዘሌዋውያን 21:11 የግርጌ ማስታወሻ፤ ሕዝቅኤል 18:20) ሰዎችም ሆኑ እንስሳት ሲሞቱ ወደ ምድር አፈር ይመለሳሉ። (መክብብ 3:19, 20) በሌላ አባባል ከሕልውና ውጭ ይሆናሉ። a

 እንስሳት ኃጢአት ሊፈጽሙ ይችላሉ?

 አይችሉም። ኃጢአት የሚባለው የአምላክን ትእዛዛት የሚጻረር ነገር ማሰብ ወይም መፈጸም ነው። አንድ ፍጥረት ኃጢአት ለመሥራት፣ የማሰብ ችሎታውን ተጠቅሞ ውሳኔ ማድረግ መቻል አለበት፤ እንስሳት ደግሞ እንዲህ ያለ ችሎታ የላቸውም። እንስሳት ውስን በሆነው የሕይወት ዘመናቸው ውስጥ አብዛኛውን ነገር የሚያደርጉት በደመ ነፍስ ነው። (2 ጴጥሮስ 2:12) ኃጢአት ባይሠሩም የሕይወት ዘመናቸው ሲያበቃ ይሞታሉ።

 እንስሳትን በጭካኔ መያዝ ተገቢ ነው?

 አይደለም። አምላክ ለሰዎች በእንስሳት ላይ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል፤ ያም ቢሆን እነሱን የማሠቃየት መብት አልተሰጣቸውም። (ዘፍጥረት 1:28፤ መዝሙር 8:6-8) አምላክ ትናንሽ ወፎችን ጨምሮ ለእያንዳንዱ እንስሳ ያስባል። (ዮናስ 4:11፤ ማቴዎስ 10:29) ሕዝቦቹም እንስሳትን በደግነት እንዲይዙ ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል።—ዘፀአት 23:12፤ ዘዳግም 25:4፤ ምሳሌ 12:10

a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 6 ተመልከት።