በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የቱሪን ከፈን—ኢየሱስ የተገነዘው በዚህ ጨርቅ ነበር?

የቱሪን ከፈን—ኢየሱስ የተገነዘው በዚህ ጨርቅ ነበር?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 የቱሪን ከፈን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም። ብዙ ሰዎች የቱሪን ከፈን (ሽራውድ ኦቭ ቱሪን ወይም ሲንዶኔ ዲ ቶሪኖ) ኢየሱስ ክርስቶስ የተገነዘበት ጨርቅ እንደሆነ ያስባሉ። በዚህም የተነሳ አንዳንዶች ይህን ከፈን ወይም መግነዝ፣ እጅግ ቅዱስ ከሆኑት የሕዝበ ክርስትና ቅርሶች አንዱ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ከፈኑ በቱሪን፣ ጣሊያን በሚገኝ ካቴድራል ውስጥ ጉዳት እንዳይደርስበት በሚከላከል የተራቀቀ መሣሪያ ተከልሎ ተቀምጧል።

 የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ስለ ቱሪን ከፈን የሚነገሩትን ሐሳቦች ይደግፋሉ? አይደግፉም።

 ከፈኑን በተመለከተ የሚነገሩ ሆኖም ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር የማይስማሙ ሦስት ሐሳቦችን እስቲ እንመልከት።

 1.   ከፈኑ 442 ሴንቲ ሜትር በ113 ሴንቲ ሜትር የሚሆን ወጥ ጨርቅ ሲሆን 8 ሴንቲ ሜትር የሚሆን ጨርቅ ተቀጥሎበታል።

   መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? የኢየሱስ አስከሬን የተጠቀለለው በተለያዩ የበፍታ ጨርቆች እንጂ አንድ ወጥ በሆነ ጨርቅ አይደለም። ራሱ ወይም ጭንቅላቱ የተጠቀለለው በተለየ ጨርቅ ነበር። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ከሐዋርያቱ መካከል አንዱ፣ ባዶ ወደሆነው መቃብር ሲመጣ ‘የበፍታ ጨርቆቹን በዚያ ተቀምጠው አይቷል።’ ጥቅሱ ቀጥሎ እንደሚገልጸው “በራሱ ላይ የነበረው ጨርቅ፣ ከመግነዝ ጨርቆቹ ጋር ሳይሆን ለብቻው ተጠቅልሎ አንድ ቦታ ላይ ተቀምጦ” ነበር።—ዮሐንስ 20:6, 7

 2.   ከፈኑ ላይ የደም ነጠብጣብ የሚታይ ሲሆን ይህም የሆነው አስከሬኑ ሳይታጠብ ስለተገነዘ እንደሆነ ይታሰባል።

   መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ኢየሱስ ሲሞት ደቀ መዛሙርቱ አስከሬኑን “በአይሁዳውያን የአገናነዝ ልማድ መሠረት” ገንዘውታል። (ዮሐንስ 19:39-42) የአይሁዳውያን ልማድ አስከሬኑን ማጠብን እንዲሁም ከመቀበሩ በፊት ዘይቶችንና ጥሩ መዓዛ ያላቸው ቅመሞችን መቀባትን ይጨምራል። (ማቴዎስ 26:12፤ የሐዋርያት ሥራ 9:37) በመሆኑም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አስከሬኑን ከመገነዛቸው በፊት አጥበውት መሆን አለበት።

 3.   ከፈኑ ላይ በቁመቱ የተጋደመ ሰው ቅርጽ ይታያል፤ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚገልጸው ‘ጨርቁ በቁመቱ ተዘርግቶ አስከሬኑ ከተጋደመበት በኋላ በቀረው ጨርቅ ከራሱ ጀምሮ መላ ሰውነቱ የተሸፈነ’ ይመስላል።

   መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስለ ሞቱና መቃብሩ ባዶ ሆኖ ስለመገኘቱ ይነጋገሩ እንደነበር ዘገባው ይገልጻል፤ ከዚህም ሌላ የዓይን ምሥክር የነበሩት ሴቶች “በተአምር የተገለጡላቸውንና እሱ ሕያው እንደሆነ የነገሯቸውን መላእክት እንዳዩ” መግለጻቸውን ደቀ መዛሙርቱ ተናግረዋል። (ሉቃስ 24:15-24) የቱሪን ከፈን በኢየሱስ መቃብር ውስጥ ቢገኝ ኖሮ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ከፈኑና በጨርቁ ላይ ስለሚታየው የሰው ምስል ይወያዩ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ጉዳይ እንደተነጋገሩ አይገልጽም።

የቱሪን ከፈን ልዩ ክብር ሊሰጠው ይገባል?

 አይገባም። የቱሪን ከፈን ኢየሱስ የተገነዘበት ጨርቅ ቢሆን እንኳ ለከፈኑ ልዩ ክብር መስጠት ስህተት ነው። እንዲህ ያልንበትን ምክንያት ለማወቅ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን እንመርምር።

 1.   አስፈላጊ አይደለም። ኢየሱስ “አምላክ መንፈስ ነው፤ የሚያመልኩትም በመንፈስና በእውነት ሊያመልኩት ይገባል” ብሏል። (ዮሐንስ 4:24) የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች ሃይማኖታዊ ሥዕሎችንና ቅርጾችን አይጠቀሙም።

 2.   የተከለከለ ነው። አሥርቱ ትእዛዛት ጣዖት አምልኮን ይከለክላሉ። (ዘዳግም 5:6-10) በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ ለክርስቲያኖች “ከጣዖቶች ራቁ” የሚል መመሪያ ሰጥቷል። (1 ዮሐንስ 5:21) አንዳንዶች የቱሪንን ከፈን እንደ ጣዖት እንደማያመልኩት ከዚህ ይልቅ የእምነታቸው ምልክት እንደሆነ አድርገው እንደሚመለከቱት ይናገራሉ። ይሁንና አንድ ነገር ለየት ያለ ክብር የሚሰጠው ከሆነ ጣዖት ሆኗል ማለት ነው። a ስለዚህ አምላክን ማስደሰት የሚፈልግ ሰው የቱሪንን ከፈን ጨምሮ ለማንኛውም ነገር ልዩ አክብሮት አይሰጥም።

a ጣዖት የሚባለው ሰዎች አምልኮ የሚያቀርቡለት ምስል ወይም ቅርጽ ነው።