በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አምላክን አይቶት የሚያውቅ አለ?

አምላክን አይቶት የሚያውቅ አለ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አምላክን አይቶት የሚያውቅ ሰው የለም። (ዘፀአት 33:20፤ ዮሐንስ 1:18፤ 1 ዮሐንስ 4:12) መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ መንፈስ ነው” በማለት ይናገራል፤ መንፈስ የሆነ አካልን ደግሞ በሰብዓዊ ዓይን ማየት አይቻልም።—ዮሐንስ 4:24፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:17

 መላእክት ግን መንፈሳዊ ፍጥረታት ስለሆኑ አምላክን በቀጥታ ሊያዩት ይችላሉ። (ማቴዎስ 18:10) በተጨማሪም በሰማይ የመኖር ተስፋ ያላቸው አንዳንድ የሰው ልጆች ከሞቱ በኋላ መንፈሳዊ አካል ይዘው በመነሳት ወደ ሰማይ ስለሚሄዱ አምላክን ማየት ይችላሉ።—ፊልጵስዩስ 3:20, 21፤ 1 ዮሐንስ 3:2

በአሁኑ ጊዜ አምላክን “ማየት” የምንችለው እንዴት ነው?

 ማየት የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ይኸውም የእውቀት ብርሃን ማግኘትን ለማመልከት ነው። (ኢሳይያስ 6:10፤ ኤርምያስ 5:21፤ ዮሐንስ 9:39-41) ከዚህ አንጻር አንድ ሰው በአሁኑ ጊዜም እንኳ ‘በልቡ ዓይኖች’ አምላክን ማየት ይችላል፤ ግለሰቡ እንዲህ ማድረግ እንዲችል ስለ አምላክ እንዲሁም ስለ ባሕርያቱ በማወቅ እምነት ማዳበር ይኖርበታል። (ኤፌሶን 1:18) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን እምነት ለማዳበር የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይጠቁመናል።

  •   አምላክ የፈጠራቸውን ነገሮች በመመልከት ስለ ፍቅሩና ስለ ልግስናው እንዲሁም ስለ ጥበቡና ስለ ኃይሉ መማር ትችላለህ። (ሮም 1:20) ታማኝ ሰው የነበረው ኢዮብ ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራዎች ከተነገረው በኋላ አምላክን በዓይኑ የተመለከተ ያህል ተሰምቶት ነበር።—ኢዮብ 42:5

  •   መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ስለ አምላክ ማወቅ ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “[አምላክን] ከፈለግኸው ታገኘዋለህ” የሚል ማረጋገጫ ይሰጥሃል።—1 ዜና መዋዕል 28:9፤ መዝሙር 119:2፤ ዮሐንስ 17:3

  •   የኢየሱስን ሕይወት በመመርመር ስለ አምላክ መማር ትችላለህ። ኢየሱስ የአባቱን የይሖዋ አምላክን ማንነት ፍጹም በሆነ መንገድ ስላንጸባረቀ “እኔን ያየ አብንም አይቷል” በማለት ሊናገር ችሏል።—ዮሐንስ 14:9

  •   አኗኗርህ አምላክን የሚያስደስት እንዲሆን አድርግ፤ እንዲህ የምታደርግ ከሆነ አምላክ ለአንተ ሲል የሚያደርጋቸውን ነገሮች መመልከት ትችላለህ። ኢየሱስ “ልባቸው ንጹሕ የሆነ ደስተኞች ናቸው፤ አምላክን ያያሉና” ብሏል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው አምላክን በሚያስደስት መንገድ ከሚኖሩ ሰዎች መካከል የተወሰኑት ከሞት ተነስተው በሰማይ ላይ ሕይወት ያገኛሉ፤ በዚያን ጊዜ “አምላክን ያያሉ።”—ማቴዎስ 5:8፤ መዝሙር 11:7

ሙሴ፣ አብርሃምና ሌሎች ሰዎች አምላክን አይተውታል?

 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ አንዳንድ ታሪኮችን ስናነብብ የሰው ልጆች አምላክን ቃል በቃል እንዳዩት ልናስብ እንችላለን፤ ይሁንና እነዚህ ታሪኮች የሚገኙበትን ዐውድ ብንመለከት አምላክ ለሰዎቹ የተገለጠላቸው በመልአክ ወይም በራእይ አማካኝነት እንደሆነ እንረዳለን።

 መላእክት።

በጥንት ዘመናት አምላክ፣ መላእክት ለሰዎች ተገልጠው በእሱ ስም እንዲናገሩ የላከባቸው ወቅቶች አሉ። (መዝሙር 103:20) ለምሳሌ ያህል አምላክ በሚነድ ቁጥቋጦ ውስጥ ሆኖ ሙሴን አነጋግሮት ነበር፤ በዚህ ጊዜ “ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፀአት 3:4, 6) ይሁንና ሙሴ በወቅቱ ያየው አምላክን አልነበረም፤ ምክንያቱም በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚጠቁመው ለሙሴ የተገለጠለት “የእግዚአብሔር መልአክ” ነው።—ዘፀአት 3:2

 በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ከሙሴ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር” ማለቱ አምላክና ሙሴ እንደ ቅርብ ወዳጆች ይነጋገሩ እንደነበር የሚጠቁም ነው። (ዘፀአት 4:10, 11፤ 33:11) ሙሴ ከአምላክ የተላከለትን መረጃ የተቀበለው “በመላእክት አማካኝነት” ስለሆነ የአምላክን ፊት አይቶ አያውቅም። (ገላትያ 3:19፤ የሐዋርያት ሥራ 7:53) ያም ቢሆን ሙሴ በአምላክ ላይ የነበረው እምነት በጣም ጠንካራ ስለነበር “የማይታየውን [አምላክ] እንደሚያየው አድርጎ” እንደተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ዕብራውያን 11:27

 አምላክ አብርሃምንም ከሙሴ ጋር የተነጋገረበትን መንገድ ተጠቅሞ ይኸውም በመላእክት አማካኝነት አናግሮታል። እርግጥ ነው፣ ታሪኩን እንዲሁ ከላይ ከላይ ስናነብ አብርሃም አምላክን ቃል በቃል እንዳየው እናስብ ይሆናል። (ዘፍጥረት 18:1, 33) ይሁንና ከዐውዱ መመልከት እንደምንችለው ወደ አብርሃም ተልከው የመጡት “ሦስት ሰዎች” ከአምላክ የተላኩ መላእክት ናቸው። አብርሃም ሰዎቹ የአምላክ ወኪሎች እንደሆኑ ስለተገነዘበ እነሱን ያነጋገረው ይሖዋን በቀጥታ እያናገረ እንዳለ አድርጎ ነው።—ዘፍጥረት 18:2, 3, 22, 32፤ 19:1

 ራእይ።

በተጨማሪም አምላክ በራእዮች አማካኝነት ይኸውም በሰዎች አእምሮ ውስጥ ምስሎች እንዲፈጠሩ በማድረግ ለሰው ልጆች ተገልጧል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ሙሴና አንዳንድ እስራኤላውያን ‘የእስራኤልን አምላክ እንዳዩ’ የሚናገረው ‘አምላክን በራእይ ስለተመለከቱ’ ነው። (ዘፀአት 24:9-11 NW) በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ነቢያት ‘አምላክን እንዳዩ’ የሚገልጽ ሐሳብ ይዟል። (ኢሳይያስ 6:1፤ ዳንኤል 7:9፤ አሞጽ 9:1) ከጥቅሶቹ ዐውድ መረዳት እንደሚቻለው ነቢያቱ አምላክን ያዩት ቃል በቃል ሳይሆን በራእይ አማካኝነት ነው።—ኢሳይያስ 1:1፤ ዳንኤል 7:2፤ አሞጽ 1:1 NW