በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

“አልፋና ኦሜጋ” ማን ወይም ምንድን ነው?

“አልፋና ኦሜጋ” ማን ወይም ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 “አልፋና ኦሜጋ” የሚለው መጠሪያ የሚያመለክተው ሁሉን ቻይ የሆነውን ይሖዋን ነው። ይህ መጠሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሦስት ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል።—ራእይ 1:8፤ 21:6፤ 22:13 a

አምላክ ራሱን “አልፋና ኦሜጋ” በማለት የጠራው ለምንድን ነው?

 አልፋና ኦሜጋ፣ የራእይን መጽሐፍ ጨምሮ በተለምዶ ‘አዲስ ኪዳን’ ተብለው የሚጠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተጻፉበት የግሪክኛ ቋንቋ የመጀመሪያና የመጨረሻ ፊደላት ናቸው። እነዚህ ፊደላት በግሪክኛ ፊደላት ቅደም ተከተል ውስጥ ያላቸው አቀማመጥ ይሖዋ ብቻ የመጀመሪያና የመጨረሻ መሆኑን ለማስረዳት ያገለግላል። (ራእይ 21:6) ይሖዋ ከመጀመሪያው አንስቶ ሁሉን ቻይ አምላክ ነበር፤ ወደፊትም ለዘላለም ሁሉን ቻይ አምላክ ነው። “ከዘላለም እስከ ዘላለም” የሚኖረው እሱ ብቻ ነው።—መዝሙር 90:2

“የመጀመሪያውና የመጨረሻው” የተባለው ማን ነው?

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ አገላለጽ ይሖዋ አምላክንም ሆነ ልጁ ኢየሱስን ለማመልከት ተሠርቶበታል፤ ሆኖም ይህ አገላለጽ የተሠራበት በተመሳሳይ መንገድ አይደለም። እስቲ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት።

  •   ይሖዋ በኢሳይያስ 44:6 ላይ “የመጀመሪያው እኔ ነኝ፤ የመጨረሻውም እኔ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም” በማለት ተናግሯል። ይሖዋ ይህን ሲል ለዘላለም እውነተኛ አምላክ የሆነው እሱ ብቻ እንደሆነና ከእሱ ሌላ ማንም እንደሌለ መግለጹ ነው። (ዘዳግም 4:35, 39) በመሆኑም በዚህ ጥቅስ ላይ “የመጀመሪያውና የመጨረሻው” የሚለው አገላለጽ “አልፋና ኦሜጋ” ከሚለው መጠሪያ ጋር ተመሳሳይ ትርጉም አለው።

  •   በተጨማሪም “የመጀመሪያውና [አልፋ ሳይሆን ፕሮቶስ] የመጨረሻው [ኦሜጋ ሳይሆን ኤስክሃቶስ]” የሚለው አገላለጽ በራእይ 1:17, 18 እና 2:8 ላይ ይገኛል። እነዚህ ጥቅሶች የሚናገሩት፣ መጀመሪያ ስለሞተ ሆኖም ከጊዜ በኋላ ስለተነሳ አካል ነው። አምላክ ደግሞ መቼም ቢሆን ሞቶ ስለማያውቅ እነዚህ ጥቅሶች እሱን የሚያመለክቱ አይደሉም። (ዕንባቆም 1:12) ኢየሱስ ግን ሞቶ የነበረ ሲሆን በኋላም ከሞት ተነስቷል። (የሐዋርያት ሥራ 3:13-15) ኢየሱስ በሰማይ የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት ያገኘ የመጀመሪያው ሰው ነው፤ አሁን በሰማይ የሚኖረው “ለዘላለም” ነው። (ራእይ 1:18፤ ቆላስይስ 1:18) ከዚያ በኋላ ትንሣኤ የሚያገኙትን ሰዎች በሙሉ የሚያስነሳው ኢየሱስ ነው። (ዮሐንስ 6:40, 44) በመሆኑም ይሖዋ በቀጥታ ያስነሳው የመጨረሻው ሰው ኢየሱስ ነው ማለት ነው። (የሐዋርያት ሥራ 10:40) ከዚህ አንጻር ኢየሱስ “የመጀመሪያውና የመጨረሻው” ተብሎ ሊጠራ ይችላል።

ራእይ 22:13 ኢየሱስ “አልፋና ኦሜጋ” እንደሆነ ያሳያል?

 አያሳይም። በራእይ 22:13 ላይ እየተናገረ ያለው ማን እንደሆነ በግልጽ አልተጠቀሰም፤ በዚህ ምዕራፍ ላይ ደግሞ የተለያዩ አካላት የተናገሯቸው ሐሳቦች ይገኛሉ። ፕሮፌሰር ዊልያም ባርክሌይ ስለዚህ የራእይ መጽሐፍ ክፍል ሲናገሩ “ሐሳቦቹ የተጻፉት ትክክለኛውን ቅደም ተከተል በጠበቀ መንገድ አይደለም፤ . . . ማን እየተናገረ እንዳለ በእርግጠኝነት ማወቅም በጣም አስቸጋሪ ነው” ብለዋል። (ዘ ሪቬሌሽን ኦቭ ጆን ጥራዝ 2፣ ተሻሽሎ የቀረበ፣ ገጽ 223) በመሆኑም በራእይ 22:13 ላይ የሚገኘው “አልፋና ኦሜጋ” የሚለው መጠሪያ፣ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ባሉ ሌሎች ቦታዎች ላይ የተጠቀሰውን ይሖዋ አምላክን የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል።

a በኪንግ ጄምስ ቨርዥን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ ራእይ 1:11 ላይ “አልፋና ኦሜጋ” የሚለው መጠሪያ ለአራተኛ ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። ሆኖም ይህ ሐሳብ ጥንታዊ በሆኑ በእጅ የተገለበጡ ግሪክኛ ጽሑፎች ውስጥ ስለማይገኝ አብዛኞቹ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ከትርጉሞቻቸው ውስጥ አውጥተውታል፤ ይህ መጠሪያ የተጨመረው ከጊዜ በኋላ በተዘጋጁ ቅጂዎች ውስጥ እንደሆነ ግልጽ ነው።