በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ናዚዎች ያደረሱት እልቂት የተከሰተው ለምንድን ነው? አምላክ ጣልቃ ገብቶ ያላስቆመውስ ለምንድን ነው?

ናዚዎች ያደረሱት እልቂት የተከሰተው ለምንድን ነው? አምላክ ጣልቃ ገብቶ ያላስቆመውስ ለምንድን ነው?

 እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን የሚያነሱ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ አስከፊ መከራ የደረሰባቸው ሲሆን ፍላጎታቸው የጥያቄዎቹን መልስ ማግኘት ብቻ ሳይሆን መጽናኛ ማግኘትም ጭምር ነው። ሌሎች ደግሞ ናዚዎች ያደረሱት ይህ እልቂት፣ የሰው ልጅ የደረሰበትን የመጨረሻ የክፋት ደረጃ የሚያሳይ ድርጊት እንደሆነ ይቆጥሩታል፤ በመሆኑም በአምላክ ላይ ያላቸው እምነት ተሸርሽሯል።

ስለ አምላክና ናዚዎች ስላደረሱት እልቂት አንዳንድ ሰዎች ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

የተሳሳተ አመለካከት፦ አምላክ ይህ እልቂት እንዲደርስ የፈቀደው ለምን እንደሆነ መጠየቅ ስህተት ነው።

 እውነታ፦ ጠንካራ እምነት የነበራቸው ሰዎች እንኳ አምላክ ክፋት እንዲደርስ የፈቀደው ለምን እንደሆነ ጥያቄ አንስተዋል? ለምሳሌ ነብዩ ዕንባቆም “እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ?” የሚል ጥያቄ ለአምላክ አቅርቧል፤ አክሎም “ጥፋትና ግፍ በፊቴ አለ፤ ጠብና ግጭት በዝቶአል” ብሏል። (ዕንባቆም 1:3) አምላክ ዕንባቆምን ከመገሠጽ ይልቅ ያቀረባቸውን ጥያቄዎች ሁላችንም እንድናነባቸው ሲል ተመዝግበው እንዲቀመጡልን አድርጓል።

የተሳሳተ አመለካከት፦ አምላክ በሰዎች ላይ የሚደርሰው መከራ አያሳስበውም።

 እውነታው፦ አምላክ ክፋትንና በክፋት ምክንያት የሚከሰተውን መከራ ይጠላል። (ምሳሌ 6:16-19) ጥንት በኖኅ ዘመን በምድር ላይ ዓመፅ በመስፋፋቱ ምክንያት አምላክ ‘ልቡ እጅግ አዝኖ’ ነበር። (ዘፍጥረት 6:5, 6) በናዚዎች ለተጨፈጨፉ ሰዎችም በጣም አዝኖ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።​—ሚልክያስ 3:6

የተሳሳተ አመለካከት፦ ናዚዎች ያደረሱት እልቂት አምላክ አይሁዳውያንን ለመቅጣት አስቦ ያደረገው ነገር ነው።

 እውነታው፦ አምላክ በአንደኛው መቶ ዘመን ኢየሩሳሌም በሮማውያን እንድትጠፋ ፈቅዷል። (ማቴዎስ 23:37 እስከ 24:2) ከዚያን ጊዜ ወዲህ ግን አምላክ ለየትኛውም ብሔር የተለየ ሞገስ አላሳየም፤ እንዲሁም የትኛውንም ብሔር አላጠፋም። በእርግጥም በአምላክ እይታ “በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ምንም ልዩነት የለም።”​—ሮም 10:12 የታረመው የ1980 ትርጉም

የተሳሳተ አመለካከት፦ አፍቃሪና ሁሉን ቻይ አምላክ ካለ የናዚዎች ጭፍጨፋ እንዳይደርስ ማስቀረት ይችል ነበር።

 እውነታው፦ አምላክ መቼም ቢሆን የመከራ መንስኤ ባይሆንም ለጊዜው መከራ እንዲደርስ ግን ፈቅዷል።—ያዕቆብ 1:13፤ 5:11

አምላክ ናዚዎች ያካሄዱት ጭፍጨፋ እንዳይደርስ ያልተከላከለው ለምንድን ነው?

 አምላክ ናዚዎች ያካሄዱት ጭፍጨፋ እንዳይደርስ ያልተከላከለበት ምክንያት በሁሉም ሰዎች ላይ መከራ እንዲደርስ ከፈቀደበት ምክንያት ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ይኸውም ከረጅም ጊዜ በፊት ለተነሳ ጥያቄ መልስ ለማስገኘት ነው። በአሁኑ ጊዜ ዓለምን እየገዛ ያለው አምላክ ሳይሆን ዲያብሎስ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (ሉቃስ 4:1, 2, 6፤ ዮሐንስ 12:31) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሁለት መሠረታዊ እውነቶች አምላክ ናዚዎች ያካሄዱት ጭፍጨፋ እንዲደርስ የፈቀደበትን ምክንያት ግልጽ ያደርጉልናል።

  1.   አምላክ የሰው ልጆችን የፈጠረው የመምረጥ ነፃነት እንዲኖራቸው አድርጎ ነው። አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ማለትም አዳምንና ሔዋንን ሲፈጥር ከእነሱ የሚፈልገውን ነገር ነግሯቸው የነበረ ቢሆንም እንዲታዘዙ ግን አላስገደዳቸውም። አዳምና ሔዋን ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር በራሳቸው ወስነዋል፤ እነሱም ሆኑ ከእነሱ በኋላ የኖሩ በርካታ ሰዎች ያደረጓቸው መጥፎ ምርጫዎች በሰው ዘር ላይ አስከፊ መዘዝ አስከትለዋል። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:6፤ ሮም 5:12) ስቴትመንት ኦቭ ፕሪንስፕልስ ኦቭ ኮንሰርቨቲቭ ጁዳይዝም የተባለው መጽሐፍ ሁኔታውን ጥሩ አድርጎ ገልጾታል፦ “በዓለም ላይ ያለው መከራ ዋነኛ መንስኤ ሰዎች የተሰጠንን የመምረጥ ነፃነት ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጠቀማችን ነው።” አምላክ ግን የመምረጥ ነፃነታችንን አልወሰደብንም፤ ከዚህ ይልቅ የሰው ልጆች ያለ እሱ ጣልቃ ገብነት ጉዳዮቻቸውን እንዲያስተካክሉ ጊዜ ሰጥቷቸዋል።

  2.   አምላክ የናዚዎች ጭፍጨፋ ያስከተለውን ጉዳት ማስተካከል ይችላል፤ ደግሞም ያስተካክለዋል። አምላክ የናዚ ጭፍጨፋ ሰለባዎችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት ለማስነሳት ቃል ገብቷል። በተጨማሪም የዚህ ጭፍጨፋ አሰቃቂ ትዝታዎች የሚያሠቃዩአቸውን ሰዎች ከስሜት ስቃይ ይገላግላቸዋል። (ኢሳይያስ 65:17፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15) አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር፣ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ዋስትና ይሆናል።​—ዮሐንስ 3:16

 ናዚዎች ካደረሱት እልቂት የተረፉት አብዛኞቹ ሰዎች አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያትና ይህ ሁኔታ ያስከተለውን ጉዳት እንደሚያስተካከል ማወቃቸው እምነታቸውን ለመጠበቅና ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት አስችሏቸዋል።