በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ትንሣኤ ምንድን ነው?

ትንሣኤ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ትንሣኤ” የሚለው ቃል የተተረጎመው አናስታሲስ ከተባለው የግሪክኛ ቃል ነው፤ ይህ ቃል “መነሳት” ወይም “እንደገና መቆም” የሚል ትርጉም አለው። አንድ ሰው ትንሣኤ አገኘ የሚባለው ከሞት ተነስቶ እንደገና በሕይወት መኖር ሲጀምር ነው፤ ግለሰቡ ከሞት የሚነሳው ከመሞቱ በፊት የነበረውን ማንነት ይዞ ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:12, 13

 “ትንሣኤ” የሚለው ቃል፣ በተለምዶ ብሉይ ኪዳን ተብለው በሚጠሩት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አይገኝም፤ ይሁን እንጂ የሞቱ ሰዎች እንደሚነሱ የሚገልጸው ትምህርት በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ በነቢዩ ሆሴዕ በኩል እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል፦ “ከመቃብር ኀይል እታደጋቸዋለሁ፤ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ።”—ሆሴዕ 13:14፤ ኢዮብ 14:13-15፤ ኢሳይያስ 26:19፤ ዳንኤል 12:2, 13

 ትንሣኤ የሚከናወነው የት ነው? አንዳንድ ሰዎች ከሞት ተነስተው በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ነገሥታት ይሆናሉ። (2 ቆሮንቶስ 5:1፤ ራእይ 5:9, 10) መጽሐፍ ቅዱስ፣ እንዲህ ዓይነቱን ትንሣኤ ‘የመጀመሪያው ትንሣኤ’ ወይም ‘ቀዳሚ የሆነው ትንሣኤ’ በማለት ይጠራዋል፤ ሁለቱም አገላለጾች ሌላ ዓይነት ትንሣኤ እንዳለ ይጠቁማሉ። (ራእይ 20:6፤ ፊልጵስዩስ 3:11) ይህ ትንሣኤ በምድር ላይ የሚከናወን ትንሣኤ ሲሆን ከሞት የሚነሱት አብዛኞቹ ሰዎች በምድር ላይ ይኖራሉ።—መዝሙር 37:29

 ትንሣኤ የሚከናወነው እንዴት ነው? አምላክ፣ ለኢየሱስ የሞቱ ሰዎችን የማስነሳት ኃይል ሰጥቶታል። (ዮሐንስ 11:25) ኢየሱስ ‘በመቃብር ውስጥ ያሉትን ሁሉ’ ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ እያንዳንዱ ሰው ከሞት የሚነሳው ከመሞቱ በፊት የነበረውን ማንነትና ትዝታ ይዞ ነው። (ዮሐንስ 5:28, 29) ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ የሚሄዱት መንፈሳዊ አካል ይሰጣቸዋል፤ ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ የሚኖሩት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ጤነኛ የሆነ ሰብዓዊ አካል ያገኛሉ።—ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6፤ 1 ቆሮንቶስ 15:42-44, 50

 ከሞት የሚነሱት እነማን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ” ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) ጻድቃን ከተባሉት መካከል እንደ ኖኅ፣ ሣራ እና አብርሃም ያሉ ታማኝ ሰዎች ይገኙበታል። (ዘፍጥረት 6:9፤ ዕብራውያን 11:11፤ ያዕቆብ 2:21) ዓመፀኛ ከተባሉት መካከል ደግሞ የአምላክን መመሪያዎች የመማር አጋጣሚ ባለማግኘታቸው እሱን መታዘዝ ያልቻሉ ሰዎች ይገኙበታል።

 ይሁን እንጂ መጥፎ አካሄዳቸውን ለመተው ፈቃደኛ ያልሆኑ ክፉ ሰዎች ከሞት አይነሱም። እንዲህ ያሉ ሰዎች ለዘላለም የሚጠፉ ሲሆን ከሞቱ በኋላ እንደገና በሕይወት የመኖር ተስፋ የላቸውም።—ማቴዎስ 23:33፤ ዕብራውያን 10:26, 27

 ትንሣኤ የሚከናወነው መቼ ነው? ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ከሞት የሚነሱት ክርስቶስ በሚገኝበት ወቅት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ ይህ ጊዜ የጀመረው በ1914 ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:21-23) ትንሣኤ በምድር ላይ የሚከናወነው ደግሞ ምድር ገነት በምትሆንበት በኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት የግዛት ዘመን ነው።—ሉቃስ 23:43፤ ራእይ 20:6, 12, 13

 ትንሣኤ እንደሚከናወን እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ ትንሣኤ የሚናገሩ በዝርዝር የተዘገቡ ዘጠኝ ታሪኮች አሉ፤ በሁሉም ዘገባዎች ላይ፣ የተፈጸመውን ትንሣኤ የተመለከቱ የዓይን ምሥክሮች እንዳሉ ተገልጿል። (1 ነገሥት 17:17-24፤ 2 ነገሥት 4:32-37፤ 13:20, 21፤ ሉቃስ 7:11-17፤ 8:40-56፤ ዮሐንስ 11:38-44፤ የሐዋርያት ሥራ 9:36-42፤ 20:7-12፤ 1 ቆሮንቶስ 15:3-6) በተለይ ኢየሱስ አልዓዛርን እንዳስነሳ የሚገልጸው ታሪክ ትኩረት የሚስብ ነው፤ ምክንያቱም አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን አልፎት የነበረ ከመሆኑም ሌላ ኢየሱስ ይህን ተአምር የፈጸመው ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ነው። (ዮሐንስ 11:39, 42) ኢየሱስን የሚቃወሙ ሰዎች እንኳ ትንሣኤው መፈጸሙን አልካዱም፤ ከዚህ ይልቅ ኢየሱስንም ሆነ አልዓዛርን ለመግደል አሴሩ።—ዮሐንስ 11:47, 53፤ 12:9-11

 አምላክ የሞቱ ሰዎችን የማስነሳት ችሎታም ሆነ ፍላጎት እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። አምላክ ታላቅ ኃይሉን ተጠቅሞ የሞቱ ሰዎችን ያስነሳል፤ በተጨማሪም አምላክ ፈጽሞ ስለማይረሳ የሚያስነሳውን እያንዳንዱን ግለሰብ በተመለከተ ዝርዝር ነገሮችን ያስታውሳል። (ኢዮብ 37:23፤ ማቴዎስ 10:30፤ ሉቃስ 20:37, 38) አምላክ የሞቱ ሰዎችን የማስነሳት ችሎታ ብቻ ሳይሆን ፍላጎትም አለው! ወደፊት የሚከናወነውን ትንሣኤ አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ሲናገር “የእጅህንም ሥራ ትናፍቃለህ” ይላል።—ኢዮብ 14:15

ሰዎች ስለ ትንሣኤ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ትንሣኤ፣ የሥጋና የነፍስ መዋሃድ ነው።

 እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ራሱ ነፍስ እንደሆነ ይናገራል፤ በመሆኑም ነፍስ አንድ ሰው ሲሞት ከውስጡ ወጥታ መኖሯን የምትቀጥል ነገር አይደለችም። (ዘፍጥረት 2:7፤ ሕዝቅኤል 18:4) ትንሣኤ የሚባለው የአንድ ሰው ነፍስና ሥጋ መዋሃድ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ግለሰቡ ሕይወት ያለው ነፍስ ሆኖ እንደገና ይፈጠራል።

 የተሳሳተ አመለካከት፦ አንዳንዶች ትንሣኤ እንዳገኙ ወዲያውኑ ይጠፋሉ።

 እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ክፉ ነገር የሠሩ” ሰዎች “ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።” (ዮሐንስ 5:29) ይሁንና ፍርድ የሚሰጣቸው፣ ከመሞታቸው በፊት ባደረጉት ነገር ሳይሆን ከሞት ከተነሱ በኋላ በሚያደርጉት ነገር ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ሙታን የሰውን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ . . . የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።” (ዮሐንስ 5:25) ከሞት ከተነሱ በኋላ የተማሩትን ነገር “የሚሰሙ” ወይም የሚታዘዙ ሰዎች ስም ‘በሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል’ ላይ ይጻፋል።—ራእይ 20:12, 13

 የተሳሳተ አመለካከት፦ አንድ ሰው ከሞት የሚነሳው ከመሞቱ በፊት የነበረውን አካል ይዞ ነው።

 እውነታው፦ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ሰውነቱ መበስበሱ አይቀርም።—መክብብ 3:19, 20