በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ዳንኤል ማን ነው?

ዳንኤል ማን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ዳንኤል በሰባተኛውና በስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረ ታዋቂ አይሁዳዊ ነቢይ ነው። አምላክ ለዳንኤል ሕልሞችን የመፍታት ችሎታ ሰጥቶታል፤ ወደፊት ስለሚፈጸሙ ክንውኖችም ራእይ አሳይቶታል። ከዚህም ሌላ በስሙ የተሰየመውን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ እንዲጽፍ በመንፈሱ መርቶታል።—ዳንኤል 1:17፤ 2:19

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዳንኤል ምን ይነግረናል?

 ዳንኤል ያደገው፣ የኢየሩሳሌም ከተማና የአይሁዳውያን ቤተ መቅደስ በሚገኙበት በይሁዳ ነው። በ617 ዓ.ዓ. የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን ተቆጣጠራት፤ ከዚያም “በምድሪቱ ውስጥ ያሉትን ታላላቅ ሰዎች ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን በግዞት ወሰደ።” (2 ነገሥት 24:15፤ ዳንኤል 1:1) በወቅቱ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እንደነበረ የሚገመተው ዳንኤልም በግዞት ከተወሰዱት አንዱ ነበር።

 ዳንኤልና የተወሰኑ ወጣት ወንዶች (ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን ጨምሮ) ለመንግሥት ሥራ ልዩ ሥልጠና እንዲያገኙ ወደ ባቢሎን ቤተ መንግሥት ተወሰዱ። ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ከእምነታቸው ጋር የሚጋጭ ነገር እንዲያደርጉ ጫና ቢደርስባቸውም ለአምላካቸው ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ጸንተዋል። (ዳንኤል 1:3-8) እነዚህ ወጣቶች የሦስት ዓመት ሥልጠና ካገኙ በኋላ ንጉሥ ናቡከደነጾር በጥበባቸውና በችሎታቸው አድናቆት ቸሯቸዋል፤ እንዲያውም “በመላ ግዛቱ ካሉት አስማተኛ ካህናትና ጠንቋዮች ሁሉ አሥር እጅ [እንደሚበልጡ]” ተናግሯል። ከዚያም ዳንኤልንና ጓደኞቹን በቤተ መንግሥት ውስጥ እንዲያገለግሉ ሾማቸው።—ዳንኤል 1:18-20

 ይህ ከሆነ ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በኋላ ዳንኤል ወደ ቤተ መንግሥቱ ተጠራ፤ በወቅቱ በ90ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። በጊዜው ባቢሎንን ይገዛ የነበረው ቤልሻዛር፣ በግድግዳው ላይ በእጅ የተጻፉትን ሚስጥራዊ ቃላት እንዲፈታ ዳንኤልን ጠየቀው። ዳንኤልም የጽሑፉን ትርጉም አምላክ ስለገለጠለት፣ ባቢሎን በሜዶ ፋርስ ድል እንደምትደረግ ተናገረ። በዚያው ሌሊት ባቢሎን ወደቀች።—ዳንኤል 5:1, 13-31

 በሜዶ ፋርስ የግዛት ዘመን ዳንኤል ከፍተኛ ባለሥልጣን ሆኖ ተሾመ፤ ንጉሥ ዳርዮስ ከዚያም የበለጠ ሥልጣን ሊሰጠው ይፈልግ ነበር። (ዳንኤል 6:1-3) ቅናት ያደረባቸው ባለሥልጣናት ዳንኤል ወደ አንበሶች ጉድጓድ እንዲጣል ሴራ ጠነሰሱ፤ ሆኖም ይሖዋ አዳነው። (ዳንኤል 6:4-23) ዳንኤል ወደ ሕይወቱ ማብቂያ ሲቃረብ አንድ መልአክ ተገልጦለት ‘እጅግ የተወደደ ሰው’ መሆኑን ሁለት ጊዜ ነግሮታል።—ዳንኤል 10:11, 19

 እነዚህ ክንውኖች ዳንኤል፦ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እምነት ያሳየ ሰው በሚለው ባለ ሁለት ክፍል የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ ላይ ሕያው በሆነ መንገድ ቀርበዋል፤ ቪዲዮውን እንድትመለከት እንጋብዝሃለን።