በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ቅዱስ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

ቅዱስ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ቅዱስ መሆን የሚለው አገላለጽ ከርኩሰት መራቅን ያመለክታል። “ቅዱስ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “መለየት” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የመጣ ነው። በመሆኑም ቅዱስ የሚለው ቃል፣ ንጹሕና ጽዱ በመሆኑ ምክንያት ለተለመደ ዓላማ ከሚውሉ ነገሮች ተለይቶ የተቀመጠን ወይም የተቀደሰን ነገር ያመለክታል።

 አምላክ በቅድስና ረገድ አቻ የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ “እንደ ይሖዋ a ያለ ቅዱስ ማንም የለም” በማለት ይናገራል። (1 ሳሙኤል 2:2) ስለዚህ የቅድስናን መሥፈርት የማውጣት መብት ያለው አምላክ ነው።

 ከአምላክ ጋር በቀጥታ የሚገናኙ፣ በተለይም ለአምልኮ የተለዩ ነገሮች በሙሉ “ቅዱስ” ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ቃል ከሚከተሉት ነገሮች ጋር አያይዞ ይገልጸዋል፦

  •   ቅዱስ ቦታዎች፦ ሙሴ በሚነደው ቁጥቋጦ አቅራቢያ በነበረበት ወቅት፣ አምላክ “የቆምክበት ስፍራ ቅዱስ መሬት ስለሆነ ጫማህን አውልቅ” ብሎታል።​—ዘፀአት 3:2-5

  •   ቅዱስ የሆኑ ክንውኖች፦ የጥንቶቹ እስራኤላውያን በየዓመቱ የሚያከብሯቸው የይሖዋ አምልኮ የሚካሄዱባቸው በዓላት “ቅዱስ ጉባኤዎች” ተብለው ይጠሩ ነበር።​—ዘሌዋውያን 23:37

  •   ቅዱስ ነገሮች፦ በኢየሩሳሌም በሚገኘው የጥንቱ ቤተ መቅደስ ውስጥ ይሖዋን ለማምለክ አገልግሎት ላይ ይውሉ የነበሩ ነገሮች “ቅዱስ ዕቃዎች” ተብለው ተጠርተዋል። (1 ነገሥት 8:4) እነዚህ ዕቃዎች ሊመለኩ የሚገቡ ነገሮች ባይሆኑም እስራኤላውያን እነዚህን የተቀደሱ ዕቃዎች በታላቅ አክብሮት መያዝ ይገባቸው ነበር። b

ፍጹም ያልሆነ ሰው ቅዱስ ሊሆን ይችላል?

 አዎ። አምላክ ክርስቲያኖችን “እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” በማለት አዟቸዋል። (1 ጴጥሮስ 1:16) እርግጥ ነው፣ ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች አምላክ ያወጣውን ፍጹም የቅድስና መሥፈርት መቼም ቢሆን ማሟላት አይችሉም። ያም ቢሆን የይሖዋን የጽድቅ ሕጎች የሚታዘዙ ሰዎች “ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት [ያላቸው]” ተደርገው ይቆጠራሉ። (ሮም 12:1) እንዲህ ያሉት ሰዎች በንግግራቸውም ሆነ በተግባራቸው ቅዱስ ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ‘እንድንቀደስና ከፆታ ብልግና እንድንርቅ’ እንዲሁም ‘በምግባራችን ሁሉ ቅዱሳን እንድንሆን’ የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ይታዘዛሉ።​—1 ተሰሎንቄ 4:3፤ 1 ጴጥሮስ 1:15

አንድ ሰው በአምላክ ዘንድ ያለውን ቅድስና ሊያጣ ይችላል?

 አዎ። አንድ ሰው አምላክ ያወጣውን የሥነ ምግባር መሥፈርት ቢጥስ አምላክ ግለሰቡን ከዚያ በኋላ ቅዱስ አድርጎ አይመለከተውም። ለምሳሌ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የዕብራውያን መልእክት የተጻፈው ‘ለቅዱሳን ወንድሞች’ ነው፤ ሆኖም እነዚህ ወንድሞች “ሕያው ከሆነው አምላክ በመራቅ እምነት የለሽ የሆነ ክፉ ልብ” ሊያቆጠቁጡ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃል።​—ዕብራውያን 3:1, 12

ብዙዎች ቅዱስ መሆንን በተመለከተ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ራስን በመጨቆን ቅዱስ መሆን ይቻላል።

 እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰውነትን ማሠቃየት’ ወይም ከልክ በላይ ራስን መጨቆን በአምላክ ዘንድ ‘አንዳች ፋይዳ እንደሌለው’ ይናገራል። (ቆላስይስ 2:23) ከዚህ ይልቅ አምላክ በጥሩ ነገሮች እንድንደሰት ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት እንዲሁም ተግቶ በሚሠራው ሥራ ሁሉ ደስታ ከማግኘት የተሻለ ነገር የለም። ይህ የአምላክ ስጦታ ነው” ይላል።​—መክብብ 3:13

 የተሳሳተ አመለካከት፦ አንድ ሰው ሳያገባ መኖሩ የበለጠ ቅዱስ እንዲሆን ያደርገዋል።

 እውነታው፦ አንድ ክርስቲያን ሳያገባ ለመኖር ሊመርጥ ቢችልም ሳያገባ መኖሩ በራሱ በአምላክ ፊት ቅዱስ ሆኖ ለመገኘት አይረዳውም። እርግጥ ነው፣ ሳያገቡ የሚኖሩ ሰዎች ለአምልኮ የበለጠ ትኩረት መስጠት ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:32-34) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ያገቡ ሰዎችም ቅዱስ መሆን እንደሚችሉ ይናገራል። እንዲያውም ከኢየሱስ ሐዋርያት መካከል አንዱ ይኸውም ጴጥሮስ አግብቶ ነበር።​—ማቴዎስ 8:14፤ 1 ቆሮንቶስ 9:5

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይህን ስም፣ “ቅዱስ” እንዲሁም “ቅድስና” ከሚሉት ቃላት ጋር አያይዘው ይገልጹታል።

b መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ቅዱስ የሚታዩ ነገሮችን ማምለክ እንደሌለብን ይናገራል።​—1 ቆሮንቶስ 10:14