በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ቁጥሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ትርጉም አላቸው? ኒውመሮሎጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ አለው?

ቁጥሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ትርጉም አላቸው? ኒውመሮሎጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ አለው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ቁጥሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የተለየ ትርጉም ባይኖራቸውም አንዳንድ ጊዜ ግን ምሳሌያዊ ትርጉም ይኖራቸዋል። አንድ ቁጥር ምሳሌያዊ ትርጉም ይኖረው እንደሆነ ማወቅ የሚቻለው የጥቅሱን አውድ በመመልከት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው አንዳንድ ቁጥሮችን እንደ ምሳሌ እንመልከት፦

  • 1 አንድነት። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ተከታዮቹን አስመልክቶ እንዲህ ሲል ወደ አምላክ ጸልዮአል፦ “ይህን ልመና የማቀርበውም ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ ነው፤ አባት ሆይ፣ አንተ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለህና እኔም ከአንተ ጋር አንድነት እንዳለኝ ሁሉ እነሱም ከእኛ ጋር አንድነት እንዲኖራቸው . . . ነው።”​—ዮሐንስ 17:21፤ ማቴዎስ 19:6

  • 2 ሕግ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አንድ ነገር እውነት መሆኑ የሚረጋገጠው ሁለት ሰዎች በሚሰጡት ምሥክርነት ነበር። (ዘዳግም 17:6) በተመሳሳይም አንድ ራእይ ወይም ሐሳብ መደጋገሙ ጉዳዩ መፈጸሙ እንደማይቀር ያረጋግጣል። ለምሳሌ ያህል፣ ዮሴፍ የግብፁ ፈርዖን የተመለከተውን ሕልም ሲፈታ እንዲህ ብሏል፦ “ሕልሙ ለፈርዖን በሁለት መልክ በድጋሚ መታየቱ፣ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ስለ ሆነ ነው።” (ዘፍጥረት 41:32) ከትንቢቶች ጋር በተያያዘ ደግሞ “ሁለት ቀንዶች” ጥምር መንግሥትን ሊያመለክቱ ይችላሉ፤ ነቢዩ ዳንኤል ስለ ሜዶ ፋርስ መንግሥት የተመለከተውን ራእይ ለዚህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።​—ዳንኤል 8:20, 21፤ ራእይ 13:11

  • 3 የሦስት ምሥክሮች ቃል አንድ ነገር እውነት መሆኑን ይበልጥ እንደሚያረጋግጥ ሁሉ አንድ ነገር ሦስት ጊዜ መደጋገሙ ለጉዳዩ ክብደት ለመስጠት ወይም ጉዳዩን ለማጉላት ይረዳል።​—ሕዝቅኤል 21:27፤ የሐዋርያት ሥራ 10:9-16፤ ራእይ 4:8፤ 8:13

  • 4 አንድ ነገር ሙሉ በሙሉ ዓላማውን እንደሚፈጽም ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል፣ “አራቱን የምድር ነፋሳት” የሚለው አገላለጽ ከአራቱ አቅጣጫዎች ማለትም መላውን ምድር የሚነካና ከሁሉም አቅጣጫ የሚመጣን ጥፋት ያመለክታል።​—ራእይ 7:1፤ 21:16፤ ኢሳይያስ 11:12

  • 6 ስድስት ቁጥር ከሰባት በአንድ ያንሳል፤ ሰባት ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ሙላትን ያመለክታል። በመሆኑም ስድስት ፍጹም ያልሆነንና የጎደለን ነገር ያመለክታል፤ አሊያም ደግሞ ከአምላክ ጠላቶች ጋር በተያያዘ ይሠራበታል።​—1 ዜና መዋዕል 20:6፤ ዳንኤል 3:1፤ ራእይ 13:18

  • 7 ይህ ቁጥር አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራበት ሙላትን ለማመልከት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን ኢያሪኮን ለሰባት ተከታታይ ቀናት እንዲዞሯት፣ በሰባተኛው ቀን ደግሞ ሰባት ጊዜ እንዲዞሯት አምላክ አዝዟቸው ነበር። (ኢያሱ 6:15) መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰባት ቁጥር በዚህ መንገድ ጥቅም ላይ የዋለባቸውን በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። (ዘሌዋውያን 4:6፤ 25:8፤ 26:18፤ መዝሙር 119:164፤ ራእይ 1:20፤ 13:1፤ 17:10) ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ወንድሙን ይቅር ማለት ያለበት ምን ያህል ጊዜ እንደሆነ ሲነግረው “እስከ ሰባ ሰባት ጊዜ እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” ብሎታል፤ “ሰባት” ቁጥር መደጋገሙ ይቅርታው “ገደብ የሌለው” መሆኑን ያሳያል።​—ማቴዎስ 18:21, 22

  • 10 ይህ ቁጥር አንድን ነገር ሙሉ በሙሉ ለመወከል ሊሠራበት ይችላል።​—ዘፀአት 34:28፤ ሉቃስ 19:13፤ ራእይ 2:10

  • 12 ይህ ቁጥር የተሟላ መለኮታዊ ዝግጅትን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ሰማይ በተመለከተው ራእይ ላይ የተገለጸው ከተማ “አሥራ ሁለት የመሠረት ድንጋዮች ነበሩት፤ በእነሱም ላይ የአሥራ ሁለቱ . . . ሐዋርያት አሥራ ሁለት ስሞች ተጽፈው ነበር።” (ራእይ 21:14፤ ዘፍጥረት 49:28) የ12 ብዜቶችም ተመሳሳይ ትርጉም ሊኖራቸው ይችላል።​—ራእይ 4:4፤ 7:4-8

  • 40 በአንዳንድ ጥቅሶች ላይ የቅጣት ወይም የፍርድ ጊዜ ከ40 ቁጥር ጋር ተያይዟል።​—ዘፍጥረት 7:4፤ ሕዝቅኤል 29:11, 12

ኒውመሮሎጂ እና ጂሜትሪያ

ኒውመሮሎጂ የሚያጠናው ቁጥሮች ያላቸውን ትርጉም እንዲሁም አንድ ላይ ሲሆኑና ሲደመሩ የሚኖራቸውን ትርጉም ነው፤ ቁጥሮቹ እንዲህ ያለ ትርጉም የሚሰጣቸው ከጥንቆላ አንጻር ነው። ይሁንና ቁጥሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያላቸው ምሳሌያዊ ትርጉም ከኒውመሮሊጂ የተለየ ነው። የአይሁድ እምነት ምሁራን ጂሜትሪያ የተባለ ዘዴ በመጠቀም በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ለሚገኙ ፊደላት ቁጥር በመስጠት ሚስጥራዊ መልእክቶች ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። ኒውመሮሎጂ የሟርት ዓይነት በመሆኑ አምላክ ያወግዘዋል።​—ዘዳግም 18:10-12