መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቁማር ዝርዝር ነገር ባይናገርም በውስጡ ከያዛቸው መመሪያዎች በመነሳት ቁማር ኃጢአት እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን።—ኤፌሶን 5:17 *

  • ቁማር የሚጫወቱ ሰዎች እንዲህ የሚያደርጉት በስግብግብነት መንፈስ ተገፋፍተው ነው፤ አምላክ ደግሞ ይህን ባሕርይ ይጠላል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ኤፌሶን 5:3, 5) ቁማርተኞች ትርፍ ለማግኘት የሚመኙት በሌሎች ኪሳራ ነው፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የሌሎችን ንብረት መመኘትን ያወግዛል።—ዘፀአት 20:17፤ ሮም 7:7፤ 13:9, 10

  • በትንሽ ገንዘብም እንኳ ቁማር መጫወት በአንድ ሰው ልብ ውስጥ አደገኛ የሆነ የገንዘብ ፍቅር እንዲያቆጠቁጥ ሊያደርግ ይችላል።—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10

  • ቁማርተኞች አብዛኛውን ጊዜ የሚመኩት በአጉል እምነትና በዕድል ነው። ሆኖም አምላክ እንዲህ ያለውን እምነት እንደ ጣዖት አምልኮ ይመለከተዋል፤ ጣዖት አምልኮ ደግሞ ከእውነተኛው አምልኮ ጋር አብሮ ሊሄድ አይችልም።—ኢሳይያስ 65:11

  • መጽሐፍ ቅዱስ ያለምንም ልፋት የሆነ ነገር ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ ጠንክሮ መሥራትን ያበረታታል። (መክብብ 2:24፤ ኤፌሶን 4:28) የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎች ‘በድካማቸው ያገኙትን ይበላሉ።’—2 ተሰሎንቄ 3:10, 12

  • ቁማር ጤናማ ያልሆነ የፉክክር ስሜት ሊቀሰቅስ ይችላል፤ ይህ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተወግዟል።—ገላትያ 5:26

^ አን.3 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቁማር በቀጥታ የተጠቀሰው የኢየሱስን ልብስ ለመከፋፈል ዕጣ ከተጣጣሉት በሌላ አባባል ቁማር ከተጫወቱት የሮም ወታደሮች ጋር በተያያዘ ብቻ ነው።—ማቴዎስ 27:35፤ ዮሐንስ 19:23, 24