ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ ያረጋግጣሉ?

ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ ያረጋግጣሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አዎ፣ ያረጋግጣሉ። ኢየሱስ ምድር ላይ በኖረበት ወቅት “የዓለም አዳኝ” ስለሚሆነው “መሪ የሆነው መሲሕ” የተነገሩ በርካታ ትንቢቶች እንዲፈጸሙ አድርጓል። (ዳንኤል 9:25፤ 1 ዮሐንስ 4:14) ኢየሱስ፣ ከሞተ በኋላም እንኳ ስለ መሲሑ የተነገሩ ትንቢቶች እንዲፈጸሙ ማድረጉን ቀጥሎ ነበር።—መዝሙር 110:1፤ የሐዋርያት ሥራ 2:34-36

 “መሲሕ” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው?

 ማሺያክ (መሲሕ) የሚለው የዕብራይስጥ ቃል እንዲሁም ክሪስቶስ (ክርስቶስ) የሚለው የግሪክኛ ቃል ተመሳሳይ ፍቺ ያላቸው ሲሆን ሁለቱም “የተቀባ” የሚል ትርጉም አላቸው። በመሆኑም “ኢየሱስ ክርስቶስ” ማለት “የተቀባው ኢየሱስ” አሊያም “መሲሑ ኢየሱስ” ማለት ነው።

 በጥንት ዘመን አንድ ሰው ለአንድ ልዩ ሥልጣን ሲሾም ብዙውን ጊዜ በራሱ ላይ ዘይት በማፍሰስ ይቀባ ነበር። (ዘሌዋውያን 8:12፤ 1 ሳሙኤል 16:13) ኢየሱስን መሲሕ አድርጎ በመሾም ከፍተኛ ሥልጣን የሰጠው አምላክ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 2:36) ሆኖም አምላክ ኢየሱስን የቀባው በዘይት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ነው።—ማቴዎስ 3:16

 ስለ መሲሑ የተነገሩ ትንቢቶች በተለያዩ ሰዎች ላይ ሊፈጸሙ ይችላሉ?

 አይችሉም። የጣት አሻራ አንድን ግለሰብ ብቻ ለይቶ እንደሚያሳውቅ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተነገሩት ትንቢቶችም ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት በአንድ መሲሕ ወይም ክርስቶስ ላይ ብቻ ነው። ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ይዟል፦ “ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክቶችና አስደናቂ ነገሮች ያደርጋሉ።”—ማቴዎስ 24:24

 ወደፊት የሚመጣ መሲሕ ሊኖር ይችላል?

 በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ መሲሑ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው የዳዊት ዘር እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል። (መዝሙር 89:3, 4) ይሁንና የዳዊትን የዘር ሐረግ የያዙ ጥንታዊ የአይሁዳውያን መዝገቦች በአሁኑ ጊዜ አይገኙም፤ ምናልባትም እነዚህ መዝገቦች የጠፉት ሮማውያን በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምን ድል ባደረጉበት ወቅት ሊሆን ይችላል። a ከዚያ ጊዜ አንስቶ፣ ማንም ሰው የዳዊት ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል መሆኑን በማስረጃ ማረጋገጥ አልቻለም። በኢየሱስ ዘመን ግን እነዚህ መዝገቦች ስለነበሩ ጠላቶቹ እንኳ ኢየሱስ የዳዊት ዘር ስለመሆኑ ጥያቄ አላነሱም።—ማቴዎስ 22:41-46

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መሲሑ የሚናገሩ ምን ያህል ትንቢቶች ይገኛሉ?

 ስለ መሲሑ የሚገልጹ ምን ያህል ትንቢቶች እንደሚገኙ በትክክል መናገር አይቻልም። ስለ መሲሑ የሚናገሩ መሆናቸው በእርግጠኝነት የሚታወቁ ትንቢቶች እንኳ የሚቆጠሩበት መንገድ የተለያየ ነው። ለምሳሌ በኢሳይያስ 53:2-7 ላይ ስለ መሲሑ የሚናገሩ በርካታ ትንቢታዊ መግለጫዎችን እናገኛለን። አንዳንዶች ሙሉውን ሐሳብ እንደ አንድ ትንቢት ይቆጥሩታል፤ ሌሎች ደግሞ እያንዳንዱ መግለጫ እንደ አንድ ትንቢት መቆጠር እንዳለበት ያስባሉ።

 በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ስለ መሲሑ የሚናገሩ አንዳንድ ትንቢቶች

ትንቢት

የሚገኝበት ጥቅስ

ፍጻሜ

የአብርሃም ዘር ይሆናል

ዘፍጥረት 22:17, 18

ማቴዎስ 1:1

የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ዘር ይሆናል

ዘፍጥረት 17:19

ማቴዎስ 1:2

ከይሁዳ ነገድ ይወለዳል

ዘፍጥረት 49:10

ማቴዎስ 1:1, 3

በንጉሥ ዳዊት የንግሥና መስመር በኩል ይመጣል

ኢሳይያስ 9:7

ማቴዎስ 1:1

ከድንግል ይወለዳል

ኢሳይያስ 7:14

ማቴዎስ 1:18, 22, 23

በቤተልሔም ይወለዳል

ሚክያስ 5:2

ማቴዎስ 2:1, 5, 6

አማኑኤል ተብሎ ይጠራል b

ኢሳይያስ 7:14

ማቴዎስ 1:21-23

በድሃ ቤተሰብ ውስጥ ይወለዳል

ኢሳይያስ 53:2

ሉቃስ 2:7

ከተወለደ በኋላ ሕፃናት ይገደላሉ

ኤርምያስ 31:15

ማቴዎስ 2:16-18

ከግብፅ ይጠራል

ሆሴዕ 11:1

ማቴዎስ 2:13-15

የናዝሬት ሰው c ይባላል

ኢሳይያስ 11:1

ማቴዎስ 2:23

ከእሱ አስቀድሞ መልእክተኛ ይመጣል

ሚልክያስ 3:1

ማቴዎስ 11:7-10

በ29 ዓ.ም. d መሲሕ ሆኖ ይቀባል

ዳንኤል 9:25

ማቴዎስ 3:13-17

የአምላክ ልጅ እንደሆነ አምላክ ራሱ ይመሠክርለታል

መዝሙር 2:7

የሐዋርያት ሥራ 13:33, 34

ለአምላክ ቤት ቅንዓት ይኖረዋል

መዝሙር 69:9

ዮሐንስ 2:13-17

ምሥራቹን ያውጃል

ኢሳይያስ 61:1

ሉቃስ 4:16-21

ምሥክርነት በመስጠት በገሊላ ታላቅ ብርሃን ያበራል

ኢሳይያስ 9:1, 2

ማቴዎስ 4:13-16

እንደ ሙሴ ተአምራትን ይፈጽማል

ዘዳግም 18:15

የሐዋርያት ሥራ 2:22

እንደ ሙሴ የአምላክን ሐሳብ ይናገራል

ዘዳግም 18:18, 19

ዮሐንስ 12:49

በርካታ የታመሙ ሰዎችን ይፈውሳል

ኢሳይያስ 53:4

ማቴዎስ 8:16, 17

ወደ ራሱ ትኩረት አይስብም

ኢሳይያስ 42:2

ማቴዎስ 12:17, 19

ለተጎሳቆሉ ሰዎች ርኅራኄ ያሳያል

ኢሳይያስ 42:3

ማቴዎስ 12:9-20፤ ማርቆስ 6:34

የአምላክን ፍትሕ ይገልጣል

ኢሳይያስ 42:1, 4

ማቴዎስ 12:17-20

ድንቅ መካሪ ይሆናል

ኢሳይያስ 9:6, 7

ዮሐንስ 6:68

የይሖዋን ስም ያሳውቃል

መዝሙር 22:22

ዮሐንስ 17:6

በምሳሌ ተጠቅሞ ይናገራል

መዝሙር 78:2

ማቴዎስ 13:34, 35

መሪ ይሆናል

ዳንኤል 9:25

ማቴዎስ 23:10

ብዙዎች አያምኑበትም

ኢሳይያስ 53:1

ዮሐንስ 12:37, 38

የሚያሰናክል ድንጋይ ይሆናል

ኢሳይያስ 8:14, 15

ማቴዎስ 21:42-44

በሰዎች ይናቃል

መዝሙር 118:22, 23

የሐዋርያት ሥራ 4:10, 11

ያለምክንያት ይጠላል

መዝሙር 69:4

ዮሐንስ 15:24, 25

በአህያ ላይ ተቀምጦ እንደ ድል አድራጊ ወደ ኢየሩሳሌም ይገባል

ዘካርያስ 9:9

ማቴዎስ 21:4-9

ልጆች ያመሰግኑታል

መዝሙር 8:2

ማቴዎስ 21:15, 16

በይሖዋ ስም ይመጣል

መዝሙር 118:26

ዮሐንስ 12:12, 13

እምነት የጣለበት ወዳጁ ይከዳዋል

መዝሙር 41:9

ዮሐንስ 13:18

በ30 የብር ሳንቲሞች አልፎ ይሰጣል e

ዘካርያስ 11:12, 13

ማቴዎስ 26:14-16፤ 27:3-10

ወዳጆቹ ትተውት ይሄዳሉ

ዘካርያስ 13:7

ማቴዎስ 26:31, 56

በሐሰት ይመሠከርበታል

መዝሙር 35:11

ማቴዎስ 26:59-61

በከሳሾቹ ፊት ዝም ይላል

ኢሳይያስ 53:7

ማቴዎስ 27:12-14

ይተፋበታል

ኢሳይያስ 50:6

ማቴዎስ 26:67፤ 27:27, 30

ራሱ ይመታል

ሚክያስ 5:1

ማርቆስ 15:19

ይገረፋል

ኢሳይያስ 50:6

ዮሐንስ 19:1

ሰዎች ሲመቱት ራሱን አይከላከልም

ኢሳይያስ 50:6

ዮሐንስ 18:22, 23

ባለሥልጣናት ያሴሩበታል

መዝሙር 2:2

ሉቃስ 23:10-12

እጆቹና እግሮቹ ላይ ምስማር ተመቶ በእንጨት ላይ ይቸነከራል

መዝሙር 22:16

ማቴዎስ 27:35፤ ዮሐንስ 20:25

ሰዎች በልብሱ ላይ ዕጣ ይጣጣላሉ

መዝሙር 22:18

ዮሐንስ 19:23, 24

ከኃጢአተኞች ጋር ይቆጠራል

ኢሳይያስ 53:12

ማቴዎስ 27:38

ይሰደባል እንዲሁም ይፌዝበታል

መዝሙር 22:7, 8

ማቴዎስ 27:39-43

ለኃጢአተኞች ሲል መከራ ይቀበላል

ኢሳይያስ 53:5, 6

1 ጴጥሮስ 2:23-25

አምላክ የተወው ይመስላል

መዝሙር 22:1

ማርቆስ 15:34

ኮምጣጤና ሐሞት እንዲጠጣ ይሰጡታል

መዝሙር 69:21

ማቴዎስ 27:34

ከመሞቱ በፊት ይጠማል

መዝሙር 22:15

ዮሐንስ 19:28, 29

መንፈሱን ለአምላክ ይሰጣል

መዝሙር 31:5

ሉቃስ 23:46

ይሞታል

ኢሳይያስ 53:12

ማርቆስ 15:37

ኃጢአትን ለማስወገድ ሲል ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ይሰጣል

ኢሳይያስ 53:12

ማቴዎስ 20:28

አጥንቶቹ አይሰበሩም

መዝሙር 34:20

ዮሐንስ 19:31-33, 36

ይወጋል

ዘካርያስ 12:10

ዮሐንስ 19:33-35, 37

ከሀብታሞች ጋር ይቀበራል

ኢሳይያስ 53:9

ማቴዎስ 27:57-60

ከሞት ይነሳል

መዝሙር 16:10

የሐዋርያት ሥራ 2:29-31

አሳልፎ በሰጠው ሰው ቦታ ሌላ ሰው ይተካል

መዝሙር 109:8

የሐዋርያት ሥራ 1:15-20

በአምላክ ቀኝ ይቀመጣል

መዝሙር 110:1

የሐዋርያት ሥራ 2:34-36

a በማክሊንቶክ እና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “የአይሁዳውያን ነገዶችና ቤተሰቦች የትውልድ መዝገብ የጠፋው ኢየሩሳሌም በወደመችበት ጊዜ እንጂ ከዚያ በፊት እንዳልሆነ ጥርጥር የለውም።”

b አማኑኤል የሚለው የዕብራይስጥ ስም “አምላክ ከእኛ ጋር ነው” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ይህም ኢየሱስ መሲሕ በመሆን የሚጫወተውን ሚና በሚገባ ይገልጻል። ኢየሱስ በምድር ላይ መኖሩና ያከናወናቸው ነገሮች አምላክ ከአገልጋዮቹ ጋር እንደሆነ የሚያረጋግጡ ናቸው።—ሉቃስ 2:27-32፤ 7:12-16

c “የናዝሬት ሰው” የሚለው አጠራር የመጣው “ቀንበጥ” የሚል ትርጉም ካለው ኔሰር የሚል የዕብራይስጥ ቃል ሳይሆን አይቀርም።

d መሲሑ የመጣው በ29 ዓ.ም. እንደሆነ ስለሚጠቁመው የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የዳንኤል ትንቢት መሲሑ የሚመጣበትን ጊዜ አስቀድሞ የተናገረው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

e ይህ ትንቢት የሚገኘው በዘካርያስ መጽሐፍ ውስጥ ቢሆንም ማቴዎስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው “በነቢዩ ኤርምያስ” በኩል እንደሆነ ጽፏል። (ማቴዎስ 27:9) የኤርምያስ መጽሐፍ “ነቢያት” ተብሎ በሚጠራው የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ላይ አንዳንድ ጊዜ መጀመሪያ ይደረግ የነበረ ይመስላል። (ሉቃስ 24:44) ማቴዎስ “ኤርምያስ” ሲል የዘካርያስን መጽሐፍ የሚያካትተውን ይህን የቅዱሳን መጻሕፍት ስብስብ በአጠቃላይ ማመልከቱ ሳይሆን አይቀርም።