በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ጋር ይስማማል?

መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ጋር ይስማማል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አዎ፣ ይስማማል። በእርግጥ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ ማስተማሪያ መጽሐፍ አይደለም፤ ይሁንና በውስጡ ያሉት ሳይንሳዊ መረጃዎች በሙሉ ትክክለኛ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ጋር እንደሚስማማ እንዲሁም በዘመኑ የነበሩ ብዙ ሰዎች ከሚያምኑባቸው ነገሮች ፈጽሞ የተለዩ ሳይንሳዊ እውነታዎችን እንደያዘ የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

  •   አጽናፈ ዓለም መጀመሪያ አለው። (ዘፍጥረት 1:1) ከዚህ በተለየ መልኩ ብዙ የጥንት አፈ ታሪኮች፣ አጽናፈ ዓለም የተገኘው ዝብርቅርቅ ብለው የነበሩ ነገሮች በራሳቸው መልክ መልክ ሲይዙ እንደሆነ እንጂ በፍጥረት እንደሆነ አይገልጹም። ባቢሎናውያን፣ ከሁለት ውቅያኖሶች የመጡ አማልክት አጽናፈ ዓለምን እንደወለዱ ያምኑ ነበር። ሌሎች አፈ ታሪኮች ደግሞ አጽናፈ ዓለም የተገኘው ከአንድ ግዙፍ እንቁላል እንደሆነ ይናገራሉ።

  •   አጽናፈ ዓለም ምክንያታዊ በሆኑ የተፈጥሮ ሕጎች የሚመራ እንጂ አማልክት እንዳሻቸው የሚቆጣጠሩት ነገር አይደለም። (ኢዮብ 38:33፤ ኤርምያስ 33:25) በዓለም ዙሪያ የሚነገሩ የተለያዩ አፈ ታሪኮች፣ አማልክት በሰው ልጆች ላይ ድንገተኛ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ምሕረት የለሽ ክስተት እንደሚያመጡ ያስተምራሉ።

  •   ምድር የተንጠለጠለችው በባዶ ስፍራ ላይ ነው። (ኢዮብ 26:7) ብዙ የጥንት ሕዝቦች፣ ምድር ጠፍጣፋ እንደሆነች እንዲሁም በአንድ ግዙፍ አካል ወይም እንደ ጎሽ እና ኤሊ ባለ እንስሳ ላይ እንደተቀመጠች ያምኑ ነበር።

  •   ከውቅያኖሶችና ከሌሎች የውኃ ምንጮች ውኃ ከተነነ በኋላ በዝናብና በበረዶ መልክ እንደገና በመውረድ ወደ ወንዞችና ወደ ጅረቶች ይገባል። (ኢዮብ 36:27, 28፤ መክብብ 1:7፤ ኢሳይያስ 55:10፤ አሞጽ 9:6) የጥንቶቹ ግሪኮች፣ ወደ ወንዞች የሚገባው ውኃ የሚመነጨው መሬት ሥር ካለ ውቅያኖስ እንደሆነ ያምኑ ነበር፤ ይህ ሐሳብ እስከ 18ኛው መቶ ዘመን ድረስ ሰፍኖ ነበር።

  •   ተራሮችና ሸለቆዎች የሚፈጠሩት የመሬቱ አቀማመጥ ከፍና ዝቅ ሲል ነው፤ በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ ያሉት ተራሮች በአንድ ወቅት በውቅያኖስ ሥር ነበሩ። (መዝሙር 104:6, 8 NW) ከዚህ በተለየ መልኩ ብዙ አፈ ታሪኮች፣ ተራሮችን አሁን ባሉበት ሁኔታ ያስቀመጧቸው አማልክት እንደሆኑ ይናገራሉ።

  •   ጥሩ የንጽሕና አጠባበቅ ለጤና አስፈላጊ ነው። ለእስራኤል ብሔር የተሰጠው ሕግ አንድ ሰው በድን ከነካ እንዲታጠብ፣ ተላላፊ በሽታ የያዛቸው ሰዎች ከሌሎች ተገልለው እንዲቆዩ እንዲሁም የሰው ዓይነ ምድር በተገቢው መንገድ እንዲወገድ የሚገልጹ መመሪያዎችን ይዟል። (ዘሌዋውያን 11:28፤ 13:1-5፤ ዘዳግም 23:13) ከዚህ በተለየ መልኩ እነዚህ መመሪያዎች በተሰጡበት ወቅት የነበሩ ግብፃውያን ከሚጠቀሙባቸው የሕክምና ዘዴዎች አንዱ ከሰው ዓይነ ምድር ጋር የተቀየጠ ነገርን ቁስል ላይ ማድረግ ነው።

ከሳይንስ አንጻር ስህተት የሆነ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ?

 መጽሐፍ ቅዱስን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ከመረመርን የዚህ ጥያቄ መልስ ‘የለም’ የሚል እንደሆነ እንረዳለን። መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ አንጻር የሚሰጠው መረጃ ትክክለኛ እንዳልሆነ የሚታሰበው በአንዳንድ የተሳሳቱ እምነቶች የተነሳ ነው፤ ከእነዚህ መካከል የተለመዱት ከዚህ ቀጥሎ ተጠቅሰዋል፦

 የተሳሳተ እምነት፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሙሉው ጽንፈ ዓለም የ24 ሰዓት ርዝማኔ ባላቸው ስድስት ቀናት እንደተፈጠረ ይገልጻል።

 እውነታው፦ አምላክ ጽንፈ ዓለምን ወደ ሕልውና ያመጣው የፍጥረት ቀናት ከመጀመራቸው በፊት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል፤ ጊዜው ግን በውል አልተጠቀሰም። (ዘፍጥረት 1:1) በተጨማሪም በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ላይ የተጠቀሱት የፍጥረት ቀናት የሚያመለክቱት በውል ያልተገለጸን ረጅም ዘመን ነው። እንዲያውም ምድርንና ሰማይን ለመፍጠር የፈጀው ጊዜ በአጠቃላይ አንድ “ቀን” እንደሆነ የተገለጸበት ቦታም አለ።—ዘፍጥረት 2:4 የ1954 ትርጉም

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ዕፀዋት የተፈጠሩት፣ ምግባቸውን እንዲያዘጋጁ ትልቅ አስተዋጽኦ የምታደርገው ፀሐይ ከመፈጠሯ በፊት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ዘፍጥረት 1:11, 16

 እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ ከዕፀዋት በፊት “ሰማያት” እንደተፈጠሩ ይናገራል፤ “ሰማያት” የሚለው ቃል ከሚያካትታቸው ነገሮች መካከል ከዋክብት የሚገኙበት ሲሆን ከእነዚህ ከዋክብት መካከል ደግሞ ፀሐይ አንዷ ናት። (ዘፍጥረት 1:1) በፍጥረት የመጀመሪያ “ቀን” ወይም ዘመን ደብዘዝ ያለ የፀሐይ ብርሃን ወደ ምድር መምጣት ጀምሮ ነበር። የምድር ከባቢ አየር እየጠራ የሄደ ሲሆን በሦስተኛው የፍጥረት “ቀን” ከባቢ አየሩን ሰንጥቆ የሚገባው የፀሐይ ብርሃን ዕፀዋት የራሳቸውን ምግብ ለማዘጋጀት የሚያስፈልገውን ኃይል በበቂ መጠን የያዘ ሊሆን ችሏል። (ዘፍጥረት 1:3-5, 12, 13) ፀሐይ በምድር ላይ በግልጽ መታየት የጀመረችው ግን ከዚህ በኋላ ነው።—ዘፍጥረት 1:16

 የተሳሳተ አመለካከት፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፀሐይ ምድርን እንደምትዞር ይናገራል።

 እውነታው፦ መክብብ 1:5 “ፀሓይ ትወጣለች፤ ትጠልቃለችም፤ ወደምትወጣበትም ለመመለስ ትጣደፋለች” ይላል። ይሁንና ይህ ሐሳብ፣ ምድር ላይ ሆኖ ለሚመለከት ሰው ፀሐይ የምትንቀሳቀስ መስላ እንደምትታይ የሚገልጽ እንጂ ሳይንሳዊ እውነታን የሚያስተላልፍ አይደለም። ዛሬም እንኳ ምድር ፀሐይን እንደምትዞር ብናውቅም “ፀሐይ ጠለቀች” ወይም “ፀሐይ ወጣች” የሚሉ አገላለጾችን እንጠቀማለን።

 የተሳሳተ አመለካከት፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ምድር ጠፍጣፋ እንደሆነች ይናገራል።

 እውነታው፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው “እስከ ምድር ዳር ድረስ” የሚለው አገላለጽ ምድር ጠፍጣፋ እንደሆነች ወይም ጠርዝ እንዳላት የሚጠቁም አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ይህ አገላለጽ የተጠቀሰው ርቀው የሚገኙ የምድር ክፍሎችን ለማመልከት ነው። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) በተመሳሳይም “ከአራቱ የምድር ማእዘን” የሚለው አገላለጽ መላውን ምድር ለማመልከት የሚሠራበት ምሳሌያዊ አባባል ነው፤ በዛሬው ጊዜም ሰዎች ተመሳሳይ አገላለጾችን ይጠቀማሉ።—ኢሳይያስ 11:12፤ ሉቃስ 13:29

 የተሳሳተ አመለካከት፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአንድ ክብ ነገር ዙሪያ መጠን የሚታወቀው ክቡን መሃል ለመሃል የሚያቋርጠውን ርዝመት (ዳያሜትር) በሦስት በማባዛት እንደሆነ የሚጠቁም ሐሳብ አለው፤ ይሁንና ትክክለኛው ስሌት ዳያሜትሩን በ3.1416 (π) ማባዛት ነው።

 እውነታው፦ በ1 ነገሥት 7:23 እና በ2 ዜና መዋዕል 4:2 ላይ የተጠቀሰው “ክብ በርሜል” ዳያሜትሩ አሥር ክንድ እንደሆነ ሐሳቡ ይናገራል፤ የክቡ ‘ዙሪያ ሲለካ ደግሞ ሠላሳ ክንድ ሆኗል።’ እነዚህ ስሌቶች የሰፈሩት ክፍልፋይ ቁጥሮችን ቅርብ ወደሆነው ሙሉ ቁጥር በማጠጋጋት ሊሆን ይችላል። ምናልባትም የክቡ ዙሪያ የተለካው በውስጥ በኩል ሲሆን የበርሜሉ ዳያሜትር ደግሞ የጠርዙን ውፍረትም የሚጨምር ሊሆን ይችላል።