በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሲኦል ምንድን ነው? የሞቱ ሰዎች ለዘላለም የሚሠቃዩበት ቦታ ነው?

ሲኦል ምንድን ነው? የሞቱ ሰዎች ለዘላለም የሚሠቃዩበት ቦታ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ሲኦል” የሚለውን ዕብራይስጥ ቃልና በግሪክኛ ተመሳሳይ ትርጉም ያለውን “ሔዲስ” የሚለው ቃል መቃጠያ ቦታን እንደሚያመለክቱ አድርገው ይተረጉሟቸዋል፤ እርግጥ ነው፣ ሁለቱም ቃላት የሚያመለክቱት የሰው ልጆችን መቃብር ነው። (መዝሙር 16:10፤ የሐዋርያት ሥራ 2:27) ብዙ ሰዎች በገሃነመ እሳት ያምናሉ፤ ገሃነም በዚህ ገጽ ላይ ያለው ሥዕል ዓይነት ቦታ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ከዚህ የተለየ ነው።

  1. ሲኦል ውስጥ ያሉ ሰዎች ከሕልውና ውጪ በመሆናቸው ምንም ዓይነት ሥቃይ ሊሰማቸው አይችልም። “መቃብር [“ሲኦል፣” የ1954 ትርጉም] ውስጥ መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለም።”​—መክብብ 9:10

  2. ጥሩ ሰዎች ሲኦል ይገባሉ። ታማኝ ሰዎች የሆኑት ያዕቆብና ኢዮብ ሲኦል ወይም መቃብር እንደሚገቡ ተናግረዋል።​—ዘፍጥረት 37:35፤ ኢዮብ 14:13 የ1954 ትርጉም

  3. ኃጢአተኞች የሚቀጡት በእሳታማ ሲኦል ውስጥ በመሠቃየት ሳይሆን በሞት ነው። “የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷልና።”​—ሮም 6:7

  4. ዘላለማዊ ቅጣት ከአምላክ ፍትሕ ጋር አይስማማም። (ዘዳግም 32:4) የመጀመሪያው ሰው አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላ ከሕልውና ውጪ እንደሚሆን አምላክ ነግሮት ነበር፤ እንዲህ አለው፦ “ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ።” (ዘፍጥረት 3:19) አምላክ፣ አዳምን ወደ እሳታማ ሲኦል በመላክ ቀጥቶት ቢሆን ኖሮ ውሸታም ይሆን ነበር።

  5. ሰዎችን ለዘላለም ማሠቃየት በአምላክ ሐሳብ ውስጥ የሌለ ነገር ነው። አምላክ ሰዎችን በእሳታማ ሲኦል ይቀጣል የሚለው አመለካከት “አምላክ ፍቅር ነው” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ይጋጫል።​—1 ዮሐንስ 4:8፤ ኤርምያስ 7:31