መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በተለይ የቅርብ ወዳጆቻችንን በሞት ስናጣ ሰዎች ለምን እንደሚሞቱ መጠየቃችን የተለመደ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሞት የሚያስከትለው መንደፊያ ኃጢአት ነው” ይላል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:56

ሁሉም ሰዎች ኃጢአተኛ የሆኑትና የሚሞቱት ለምንድን ነው?

የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የሆኑት አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት ሞተዋል። (ዘፍጥረት 3:17-19) አምላክ “የሕይወት ምንጭ” በመሆኑ በእሱ ላይ ማመፅ ሞት ማስከተሉ ሳይታለም የተፈታ ነው።​—⁠መዝሙር 36:9፤ ዘፍጥረት 2:17

አዳም የነበረበትን ኃጢአት ለዘሮቹ በሙሉ አስተላልፏል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) ሁሉም ሰዎች የሚሞቱት ኃጢአተኞች በመሆናቸው ነው።​—⁠ሮም 3:23

ሞት የሚወገደው እንዴት ነው?

አምላክ ‘ሞትን ለዘላለም የሚውጥበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 25:8) ሞትን ለማስወገድ ግን መጀመሪያ ምንጩን ማለትም ኃጢአትን ማጥፋት ያስፈልገዋል። አምላክ ይህን የሚያደርገው ‘የዓለምን ኃጢአት በሚያስወግደው’ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነው።​—⁠ዮሐንስ 1:29፤ 1 ዮሐንስ 1:7