በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሞት አፋፍ ላይ ደርሰው የተመለሱ ሰዎች እንዳጋጠማቸው የሚናገሩት ትክክል ነው?

ሞት አፋፍ ላይ ደርሰው የተመለሱ ሰዎች እንዳጋጠማቸው የሚናገሩት ትክክል ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ሞት አፋፍ ላይ ደርሰው የነበሩ በርካታ ሰዎች ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለይታ እንደነበር ወይም ደማቅ ብርሃን አሊያም በጣም የሚያምር ቦታ መመልከታቸውን እንደሚያስታውሱ ይናገራሉ። ሪኮሌክሽንስ ኦቭ ዴዝ የተባለው መጽሐፍ ‘አንዳንዶች ይህን ሁኔታ ሌላ ዓለምን የመመልከት መብት እንደማግኘት ይቆጥሩታል’ በማለት ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ በሞት አፋፍ ላይ ደርሰው ስለሚያውቁ ሰዎች የሚናገረው ነገር ባይኖርም እነዚህ ሰዎች የተመለከቱት ነገር ከሞት በኋላ ያለውን ሕይወት የሚያመለክት እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ይዟል።

ሙታን ከሕልውና ውጪ ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ‘ምንም እንደማያውቁ’ ይናገራል። (መክብብ 9:5) ከሞትን በኋላ በሌላ ዓለም ሕያው ሆነን አንኖርም፤ ከዚህ ይልቅ ሕልውናችን ያከትማል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከሞት በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ነፍስ አለች’ የሚል ትምህርት አያስተምርም። (ሕዝቅኤል 18:4) በመሆኑም በሞት አፋፍ ላይ ደርሰው የነበሩ ሰዎች ሰማይን፣ የመሠቃያ ቦታን ወይም ሌላ ዓለምን ተመልክተው ሊሆን አይችልም።

አልዓዛር ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ምን የተናገረው ነገር አለ?

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው አልዓዛር ሞቶ ነበር፤ ከሞተ ከአራት ቀናት በኋላ ኢየሱስ ከሞት አስነስቶታል። (ዮሐንስ 11:38-44) አልዓዛር ከሞተ በኋላ በሌላ ዓለም ተመችቶት እየኖረ ከነበረ ኢየሱስ እሱን ከሞት በማስነሳት ምድር ላይ እንዲኖር ማድረጉ የጭካኔ ድርጊት ይሆን ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አልዓዛር ሞቶ በነበረበት ወቅት ስለነበረው ሁኔታ የሚናገረው ነገር የለም። አልዓዛር በሞተበት ወቅት ያጋጠመው ነገር ቢኖር ኖሮ ጉዳዩን አስመልክቶ ይናገር እንደነበር ግልጽ ነው። ትኩረት የሚስበው ደግሞ ኢየሱስ የአልዓዛርን ሞት ከእንቅልፍ ጋር ያመሳሰለው መሆኑ ነው፤ ምክንያቱም ይህ አገላለጽ አልዓዛር ሞቶ በነበረበት ወቅት በአካባቢው ስለሚከናወነው ነገር ምንም እንደማያውቅ የሚጠቁም ነው።​—ዮሐንስ 11:11-14