በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጾም ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጾም ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በጥንት ዘመን የነበሩ ሰዎች በትክክለኛው ዓላማ ተነሳስተው ሲጾሙ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ነበር። የሚጾሙት በተሳሳተ ዓላማ ተነሳስተው ከሆነ ግን ጾማቸው አምላክን አያስደስተውም ነበር። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች መጾም እንዳለባቸውም ሆነ እንደሌለባቸው አይናገርም።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ሰዎች የጾሙት ለምንድን ነው?

  •   የአምላክ እርዳታና አመራር ለማግኘት። ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ሰዎች የአምላክን እርዳታ በጠየቁበት ወቅት ያቀረቡት ልመና ልባዊ እንደሆነ ለማሳየት ጾመው ነበር። (ዕዝራ 8:21-23) ጳውሎስና በርናባስም የጉባኤ ሽማግሌዎችን በሚሾሙበት ወቅት አንዳንድ ጊዜ ይጾሙ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 14:23

  •   በአምላክ ዓላማ ላይ ትኩረት ለማድረግ። ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ለ40 ቀናት ጾሟል፤ ይህን ያደረገው በምድር ላይ በሚያከናውነው አገልግሎት የአምላክን ፈቃድ መፈጸም እንዲችል ራሱን ለማዘጋጀት ነበር።—ሉቃስ 4:1, 2

  •   ቀደም ሲል ለተፈጸመ ኃጢአት ንስሐ መግባትን ለማሳየት። አምላክ ታማኝ ላልነበሩት እስራኤላውያን “በጾም፣ በለቅሶና በዋይታ በሙሉ ልባችሁ ወደ እኔ ተመለሱ” በማለት በነቢዩ ኢዩኤል አማካኝነት ነግሯቸዋል።—ኢዩኤል 2:12-15

  •   የስርየት ቀንን ለማክበር። አምላክ ለእስራኤል ብሔር የሰጠው ሕግ እስራኤላውያን በዓመት አንዴ በሚያከብሩት የስርየት ቀን ላይ እንዲጾሙ ያዝዝ ነበር። a (ዘሌዋውያን 16:29-31) እስራኤላውያን በዚህ ቀን መጾማቸው ተገቢ ነበር፤ ምክንያቱም ኃጢአተኛ መሆናቸውንና የአምላክ ምሕረት እንደሚያስፈልጋቸው ያስታውሳቸዋል።

አንዳንድ ሰዎችን እንዲጾሙ የሚያነሳሷቸው የተሳሳቱ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

  •   የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ። ኢየሱስ አንድ ሰው ሲጾም ለሌላ ሰው መናገር እንደሌለበትና ጾም በግለሰቡና በአምላክ መካከል ብቻ ያለ ጉዳይ መሆን እንዳለበት አስተምሯል።—ማቴዎስ 6:16-18

  •   ጻድቅ መስሎ ለመታየት። አንድ ሰው መጾሙ በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊነት ረገድ ከሌሎች የበለጠ እንዲሆን አያደርገውም።—ሉቃስ 18:9-14

  •   ሆን ተብሎ የሚፈጸምን ኃጢአት ለማካካስ። (ኢሳይያስ 58:3, 4) አንድ ሰው መጾሙ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው ግለሰቡ ታዛዥ ከሆነና ለፈጸመው ኃጢአት ከልቡ ንስሐ ከገባ ብቻ ነው።

  •   ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለመፈጸም። (ኢሳይያስ 58:5-7) አንድ ወላጅ ልጆቹ ለእሱ ያላቸውን ፍቅር የሚገልጹት በእርግጥ ስለሚወዱት ሳይሆን ተገደው ቢሆን እንደሚያዝን የታወቀ ነው፤ ከአምላክ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

ክርስቲያኖች መጾም ይጠበቅባቸዋል?

 አይጠበቅባቸውም። እስራኤላውያን በስርየት ቀን እንዲጾሙ አምላክ አዟቸው ነበር፤ ሆኖም ኢየሱስ ንስሐ የገቡ ሰዎችን ኃጢአት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ካስተሰረየ በኋላ የስርየት ቀን መከበር አቁሟል። (ዕብራውያን 9:24-26፤ 1 ጴጥሮስ 3:18) ክርስቲያኖች የስርየት ቀን እንዲከበር በሚያዘው በሙሴ ሕግ ሥር አይደሉም። (ሮም 10:4፤ ቆላስይስ 2:13, 14) በመሆኑም እያንዳንዱ ክርስቲያን ለመጾምም ሆነ ላለመጾም የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይችላል።—ሮም 14:1-4

 ክርስቲያኖች ጾም የአምልኳቸው ዋነኛ ክፍል እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ጾምን ከደስታ ጋር አያይዞ አይገልጸውም። እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን የሚያመልኩት ‘ደስተኛ አምላክ’ የሆነውን ይሖዋን በመሆኑ አምልኳቸውን የሚያከናውኑት በደስታ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 1:11፤ መክብብ 3:12, 13፤ ገላትያ 5:22

ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጾም የሚናገረውን ነገር በተመለከተ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ሐዋርያው ጳውሎስ ያገቡ ክርስቲያኖች እንዲጾሙ መክሯል።—1 ቆሮንቶስ 7:5 የ1879 ትርጉም

 እውነታው፦ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች 1 ቆሮንቶስ 7:5 ላይ ጾምን አይጠቅሱም። b የመጽሐፍ ቅዱስ ገልባጮች እዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ሳይሆን ማቴዎስ 17:21፤ ማርቆስ 9:29 እና የሐዋርያት ሥራ 10:30 ላይም ስለ ጾም የሚናገር ሐሳብ ጨምረዋል። አብዛኞቹ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ስለ ጾም የሚናገሩት እነዚህ የተሳሳቱ ሐሳቦች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲወጡ አድርገዋል።

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ለ40 ቀናት በምድረ በዳ ጾሟል፤ ክርስቲያኖችም ይህን ለማሰብ ለ40 ቀን መጾም አለባቸው።

 እውነታው፦ ኢየሱስ ተከታዮቹ ለ40 ቀናት እንዲጾሙ ትእዛዝ አልሰጠም፤ የጥንቶቹ ክርስቲያኖችም ቢሆኑ የኢየሱስን የ40 ቀን ጾም ለማሰብ ብለው እንደጾሙ የሚጠቅስ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። c

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ሲያከብሩ መጾም አለባቸው።

 እውነታው፦ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሞቱን መታሰቢያ በሚያከብሩበት ጊዜ እንዲጾሙ አላዘዛቸውም። (ሉቃስ 22:14-18) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እሱ ከሞተ በኋላ እንደሚጾሙ ሲናገር ተከታዮቹ እንዲጾሙ ትእዛዝ ማስተላለፉ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ምን እንደሚከናወን መግለጹ ነበር። (ማቴዎስ 9:15) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ክርስቲያን የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ በሚያከብርበት ዕለት ከራበው በዓሉን ከማክበሩ በፊት ቤቱ ምግብ መብላት እንዳለበት ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 11:33, 34

a አምላክ ለእስራኤላውያን በስርየት ቀን ‘ራሳቸውን እንዲያጎሳቁሉ’ ነግሯቸዋል። (ዘሌዋውያን 16:29, 31) ይህ አገላለጽ ጾምን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። (ኢሳይያስ 58:3) በመሆኑም ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርዥን የተባለው ትርጉም ይህን ሐሳብ “በኃጢአታችሁ ማዘናችሁን ለማሳየት ምግብ አትብሉ” በማለት ተርጉሞታል።

b በብሩስ ሜጽገር የተዘጋጀውን ኤ ቴክስቹዋል ኮሜንታሪ ኦን ዘ ግሪክ ኒው ቴስታመንት የተባለ መጽሐፍ ሦስተኛ እትም፣ ገጽ 554 ተመልከት።

c ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ ለ40 ቀናት የሚጾመውን የሁዳዴ ጾም (በኢትዮጵያ ወደ ሁለት ወር ገደማ ነው) አመጣጥ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት ከፋሲካ በፊት የሚደረገው ጾም ከአንድ ሳምንት አይበልጥም ነበር፤ እንዲያውም በአብዛኛው የሚጾመው ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ያህል ብቻ ነበር። . . . ስለ 40 ቀን ጾም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው በኒቂያ ጉባኤ (325) አምስተኛ ቀኖና ላይ ነው፤ እርግጥ አንዳንድ ምሁራን እዚህ ላይ የተጠቀሰው የሁዳዴ ጾም መሆኑን አይቀበሉም።”—ሁለተኛ እትም፣ ጥራዝ 8፣ ገጽ 468