መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አያስተምርም። “ሪኢንካርኔሽን” የሚለው ቃልም ሆነ ጽንሰ ሐሳቡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። የሪኢንካርኔሽን ጽንሰ ሐሳብ፣ ‘ነፍስ አትሞትም’ በሚለው ትምህርት ላይ የተመሠረተ ነው። * ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ነፍስ ሲባል ግለሰቡን ራሱን እንደሚያመለክት ያስተምራል፤ በመሆኑም ነፍስ ሟች መሆኗን ይገልጻል። (ዘፍጥረት 2:7 የግርጌ ማስታወሻ፤ ሕዝቅኤል 18:4) ሰው ሲሞት፣ ከሕልውና ውጪ ይሆናል።—ዘፍጥረት 3:19፤ መክብብ 9:5, 6

በሪኢንካርኔሽን እና በትንሣኤ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የትንሣኤ ትምህርት፣ ‘ነፍስ አትሞትም’ በሚለው ሐሳብ ላይ የተመሠረተ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ፣ የሞቱ ሰዎችን በትንሣኤ ወቅት እንደገና ሕያው ያደርጋቸዋል። (ማቴዎስ 22:23, 29፤ ሥራ 24:15) የትንሣኤ ትምህርት፣ ሙታን አዲስ በሆነች ምድር ላይ ከሞት ተነስተው ዳግመኛ ሳይሞቱ መኖር እንደሚችሉ የሚናገር አስደሳች ተስፋ ይሰጣል።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3, 4.

ብዙዎች ሪኢንካርኔሽንን እና መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

የተሳሳተ አመለካከት፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ነቢዩ ኤልያስ ሌላ አካል ለብሶ መጥምቁ ዮሐንስን ሆኖ እንደመጣ ያስተምራል።

እውነታው፦ አምላክ “ነቢዩ ኤልያስን እልክላችኋለሁ” የሚል ትንቢት ያስነገረ ሲሆን ኢየሱስ ይህ ትንቢት በመጥምቁ ዮሐንስ ላይ እንደተፈጸመ ተናግሯል። (ሚልክያስ 4:5, 6፤ ማቴዎስ 11:13, 14) ሆኖም ይህ ሲባል ‘ነቢዩ ኤልያስ ሌላ አካል ለብሶ መጥምቁ ዮሐንስን ሆኖ መጥቷል’ ማለት አይደለም። ዮሐንስ ራሱ፣ እሱ ኤልያስ እንዳልሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 1:21) ከዚህ ይልቅ ዮሐንስ፣ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ በመስበክ ኤልያስ ያከናወነው ዓይነት ሥራ ሠርቷል። (1 ነገሥት 18:36, 37፤ ማቴዎስ 3:1, 2) እንዲሁም ዮሐንስ “ልክ እንደ ነቢዩ ኤልያስ ጠንካራና ኃይለኛ” ነበር።—ሉቃስ 1:13-17ጉድ ኒውስ ትራንስሌሽን

የተሳሳተ አመለካከት፦ መጽሐፍ ቅዱስ ሪኢንካርኔሽንን ‘ዳግመኛ መወለድ’ በማለት ይገልጸዋል።

እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዳግመኛ መወለድ’ የሚለው አንድ ሰው በሕይወት እያለ ዳግመኛ በመንፈስ መወለዱን ለማመልከት ነው። (ዮሐንስ 1:12, 13) እንዲህ ዓይነቱ ዳግመኛ መወለድ፣ አንድ ሰው ቀድሞ የሠራቸው ነገሮች የሚያስከትሉበትና ሊያመልጠው የማይችል ነገር ሳይሆን ከአምላክ የሚገኝ በረከት ነው፤ ይህን በረከት የሚያገኙ ሰዎች ለየት ያለ የወደፊት ተስፋ አላቸው።—ዮሐንስ 3:3፤ 1 ጴጥሮስ 1:3, 4

^ አን.3 ‘ነፍስ አትሞትም’ የሚለው ትምህርት እና የሪኢንካርኔሽን እምነት የተጀመረው በጥንቷ ባቢሎን ነበር። በኋላ ደግሞ የሕንድ ፈላስፎች የካርማን መሠረተ ትምህርት አመጡ። ብሪታኒካ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ዎርልድ ሪሊጅንስ እንደሚናገረው ካርማ “በድርጊት እና በውጤት ሕግ” ላይ የተመሠረተ ነው። “በዚህ ሕግ መሠረት አንድ ሰው በአሁኑ ሕይወቱ የሚያደርገው ነገር ዳግመኛ ሲወለድ በሚኖረው ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።”—ገጽ 913