በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ በቀል ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ በቀል ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አንድ ሰው ለደረሰበት በደል መበቀሉ ተገቢ እንደሆነ ቢሰማው እንኳ እንዲህ ማድረጉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጋር ይጋጫል። መጽሐፍ ቅዱስ “‘እሱ እንዳደረገብኝ እንዲሁ አደርግበታለሁ፤ አጸፋውን እመልሳለሁ’ አትበል” ይላል። (ምሳሌ 24:29 የግርጌ ማስታወሻ) መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች የበቀል ስሜታቸውን እንዲያሸንፉ የሚረዱ ምክሮች ይዟል።

በዚህ ርዕስ ውስጥ፦

 መበቀል ስህተት የሆነው ለምንድን ነው?

 አንድ ሰው የሚያበሳጭ ወይም የሚጎዳ ነገር ሲያደርግብህ መቆጣትህና ያ ሰው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ መፈለግህ ያለ ነገር ነው። ሆኖም ራስህ ለመበቀል መነሳትህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው ምክር ጋር ይጋጫል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

 ሰዎች ራሳቸው የበቀል እርምጃ መውሰዳቸው አምላክን ያሳዝነዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይሖዋ a አምላክ “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ብሏል። (ሮም 12:19) መጽሐፍ ቅዱስ በደል የደረሰባቸው ሰዎች ከመበቀል ይልቅ በተቻለ መጠን ጉዳዩን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱት ያበረታታል። (ሮም 12:18) ሆኖም ጉዳዩን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ያደረግከው ጥረት ሁሉ ባይሳካስ? ወይም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት የሚቻልበት መንገድ ባይኖርስ? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ የተፈጸመብንን ማንኛውንም በደል ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንደሚያስተካክለው እምነት እንዲኖረን ያበረታታናል።—መዝሙር 42:10, 11

 አምላክ ሰዎች ለጥፋታቸው ቅጣት እንዲቀበሉ የሚያደርገው እንዴት ነው?

 በአሁኑ ጊዜ አምላክ ጥፋት የሠሩ ሰዎችን የመቅጣት መብት የሰጠው ለባለሥልጣናት ነው። (ሮም 13:1-4) ወደፊት ግን እሱ ራሱ ጥፋት የሠሩ ሰዎችን ወደ ፍርድ ያመጣቸዋል፤ እንዲሁም ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን በሙሉ ለዘላለም ያስወግዳል።—ኢሳይያስ 11:4

 የሚሰማኝን የበቀል ስሜት ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?

  •   በቁጣ ገንፍለህ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጠብ። (ምሳሌ 17:27) በቁጣ ገንፍለው እርምጃ የሚወስዱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ በኋላ ላይ የሚጸጸቱበትን ነገር ያደርጋሉ። እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ቆም ብለው የሚያስቡ ሰዎች ግን ትክክለኛ ውሳኔ የማድረግ አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው።—ምሳሌ 29:11

  •   የተሟላ መረጃ ይኑርህ። (ምሳሌ 18:13) በደል የተፈጸመበት ሰው እንደሚከተለው ብሎ ራሱን መጠየቁ ጥሩ ነው፦ ‘በደል የፈጸመብኝ ሰው እንዲህ ዓይነት እርምጃ እንዲወስድ ያደረጉት እኔ የማላውቃቸው ነገሮች ይኖሩ ይሆን? ውጥረት አጋጥሞት ይሆን? ወይስ ይህን ያደረገው ባለማወቅ ነው?’ አንዳንድ ጊዜ ሆን ተብሎ እንደተፈጸመብን የምናስበው ነገር በስህተት የተፈጸመ ሊሆን ይችላል።

 ሰዎች ስለ በቀል ያላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ

 የተሳሳተ ግንዛቤ፦ መጽሐፍ ቅዱስ “ዓይን ስለ ዓይን” ስለሚል በቀልን ይፈቅዳል።—ዘሌዋውያን 24:20

 እውነታው፦ “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ለጥንት እስራኤላውያን የተሰጠው ሕግ ሰዎች በራሳቸው ተነሳስተው እንዳይበቀሉ የሚከላከል ነው። ይህ ሕግ የተሰጠው ዳኞች ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲያስተላልፉ ለመርዳት ነው። bዘዳግም 19:15-21

 የተሳሳተ ግንዛቤ፦ መጽሐፍ ቅዱስ በቀልን ስለማይፈቅድ ጥቃት ሲሰነዘርብን ራሳችንን መከላከል አንችልም።

 እውነታው፦ አንድ ሰው ጥቃት ሲሰነዘርበት ራሱን የመከላከል ወይም ለሕግ አካላት በማሳወቅ እርዳታ የመጠየቅ መብት አለው። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ በተቻለ መጠን ከጠብና የኃይል እርምጃ ከመውሰድ እንድንርቅ ይመክረናል።—ምሳሌ 17:14

a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።

b ስለዚህ ሕግ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “‘ዓይን ስለ ዓይን’ ሲባል ምን ማለት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።